Fana: At a Speed of Life!

ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ለሚያካሄደው ሕዝበ ውሳኔ 541 ሚሊየን ብር በጀት ጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ለሚያካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የ541 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የበጀት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ውስጥ ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሣኔ ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገውን 541 ሚሊየን 270 ሺህ 104 ብር ከ82 ሳንቲም ተገማች በጀት ለኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡

ቦርዱ በደቡብ ክልል ሥር የሚገኙ ስድስት ዞኖች ማለትም የጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጌዲዮ፣ ኮንሶና፣ ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም አምስት ልዩ ወረዳዎችን እነዚህም የቡርጂ፣ አማሮ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ፣ አሌ ልዩ ልዩ ወረዳዎች ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንደሚያካሂድ ይታወቃል።

ቦርዱ በተጠቀሱት ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ላይ ሕዝበ ውሣኔ በማደራጀት ውጤቱን እንዲያሳውቅ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ መጠየቁ ይታወሳል፡፡

በዚህ መሠረትም ቦርዱ የሕዝብ ውሣኔውን ለማከናወን የሚያስፈልጉ ዝርዝር ተግባራትን በማካተት የድርጊት መርኅ ግብር አዘጋጅቶ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡

በሕዝበ ውሣኔው የድርጊት መርሐ ግብር ላይ የተጠቀሱትን አጠቃላይ ተግባራት ተፈጻሚ ለማድረግም የሚያስፈልገውን በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.