Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በወንጀል ጉዳይ ላይ በትብብር ለመስራት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴርና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የፍትሕ ሚኒስቴር በወንጀል ጉዳይ ላይ በትብብር ለመስራትና ወንጀለኞችን አሳልፎ መስጠት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱን የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የፍትሕ ሚኒስትር ሼኽ አብዱላ ሱልጣን አል ኑዓይሚ በአቡዳቢ ተፈራርመዋል፡፡

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረሙት ስምምነቶች በፍትሕ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡

በቀጣይ በሀገራቱ መካከል በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ መሰል ስምምነቶችን በመፈራረም ያለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት በይበልጥ ማሳደግ ስለሚቻልበት ሁኔታ ላይም ውይይት ተደርጓል።

የፍትሕ ሚኒስትርዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው፥ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ለረጅም ጊዜያት የዘለቀ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በፍትሕ ዘርፍ የተፈረሙት ስምምነቶችም የዚህ ጠንካራና የቆየ ወዳጅነት መገለጫዎች መሆናቸውን ጠቁመው፥ በቀጣይ በአቅም ግንባታ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በሌሎች መስኮች ላይ አብሮ ለመስራት የኢትዮጵያ መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የፍትሕ ሚኒስትር ሼኽ አብዱላ ሱልጣን አል ኑዓይሚ በበኩላቸው፥ የሁለቱ አገራት የቆየ ግንኙነት በሁሉም መስኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተባበሩት ዓረብኤምሬቶች ስትራቴጂክ አጋር ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፥ ከፍትሕ ዘርፍ በተጨማሪ በሌሎች የትብብርመስኮች ላይ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሮቹ በመካከላቸው ለተፈረሙት ስምምነቶች ተፈፃሚነት ትኩረት ሰጥተው በጋራ እንደሚሰሩ መግለጻቸውንም ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.