በሃዋሳ ከተማ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ እና ባዕድ ነገር ቀላቅለው ለገበያ ባቀረቡ አካላት ላይ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በሃዋሳ ከተማ የኮሮና ቫይረስን መከሰት ምክንያት በማድረግ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ እና ባዕድ ነገር በመቀላቀል ለገበያ ሲያቀርቡ በነበሩ አካላት ላይ እርምጃ ተወሰደ።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ደቡብ ቅርንጫፍ፣ የደቡብ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪና የሀዋሳ ከተማ ንግድ መምሪያ ባደረጉት ድንገተኛ አሰሳ ነው እርምጃ ሊወሰድባቸው የቻለው።
በዚህም በሁለት የመድኃኒት መደብሮች፣ 22 የንግድ ተቋማትና ሁለት የነዳጅ ማደያዎች ታሽገዋል።
የሀዋሳ ከተማ ንግድ መምሪያ የሸማቾች አገልግሎት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ በየነ ባልቻ ህገ ወጦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ህብረተሰቡም ጥቆማ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በቢኒያም ሲሳይ