Fana: At a Speed of Life!

የቻይና ዓለም አቀፍ የልማት ኢኒሼቲቭ የልማት ግቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ወሳኝ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለመተግበር ትብብር እና አጋርነት ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናገሩ፡፡

አቶ ደመቀ በኒውዮርክ ከተማ እየተካሄደ ካለው 77ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የዓለም አቀፍ ልማት ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ድህነትን ለማጥፋትና ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ታቅዶ በቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የተወጠነውን ዓለም አቀፉን የልማት ኢኒሼቲቭ አድንቀዋል።

የኮቪድ19 ወረርሽኝ፣ አካባቢያዊ የፖለቲካ ውጥረት እና የምግብ እና የነዳጅ ቀውስ፥ ከዓለም አቀፉ የልማት ኢኒሼቲቭ አንጻር ትብብርን አስፈላጊ አድርገውታልም ነው ያሉት።

አያይዘውም አሁን ላይ ዓለማችን የተጋፈጠቻቸው ተግዳሮቶች በባለብዙ ወገን ማዕቀፍ ውስጥ ፍትሃዊ እና አካታችነትን ባማከለ መልኩ የትብብር አስፈላጊነት ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በበኩላቸው፥ ቤጂንግ 4 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ፕሮጀክቶች ለመተግበር ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

ቡድኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 2030 የዘላቂ ልማት ግቦችን ከማስተዋወቅ አንጻር ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ዕቅዶች ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በጋራ መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ደግሞ፥ ሁለንተናዊው ዓለም አቀፍ የልማት ኢኒሼቲቭ የጋራ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚረዳ አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ሽግግሩን ለማፋጠን በሚደረግ ጥረት አይተኛ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.