Fana: At a Speed of Life!

በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የመጠጥ ውሃ ተቋማትና መጸዳጃ ቤቶች ይገነባሉ – የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በ2015 ዓ.ም በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የመጠጥ ውሃ ተቋማት፣ የማህበረሰብና የጋራ መጸዳጃ ቤቶች ለመገንባት እየሠራ መሆኑን ገለጸ፡፡

ፕሮጀክቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ነዋሪዎች በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ እንደሚተገበር ተገልጿል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ተስፋዬ አቡቡ እንደገለጹት÷ ቢሮው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የሕዝብና የጋራ መጸዳጃ ቤቶች፣ የቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃና ማከሚያ ተቋማት ጥናት፣ ዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች በመከወን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው፡፡

ተግባራቱ በልዩ ልዩ ረጅ ድርጅቶች የበጀት ድጋፍ የሚሠሩ ቢሆንም÷ በዓለም ባንክ የተመደበው 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለሥራው ውጤታማነት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ነው ያሉት፡፡

በባሕር ዳር፣ ደሴ፣ ጎንደርና ደብረ ብርሃን ከተሞች 58 የሕዝብ እና 87 የጋራ መጸዳጃ ቤት ግንባታ፣ በፌደራል መንግሥት ድጋፍ በኮምቦልቻና ደብረ ማርቆስ ከተሞች የቆሻሻ ፍሳሽ ማከሚያ  እና ማጠራቀሚያ ጥናት፣ ዲዛይንና ግንባታ ሥራ በማከናወን ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት በተጀመሩና በ2015 ተጀምረው በሚጠናቀቁ ሥራዎች በክልሉ 385 ሺህ 231 የከተማ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.