Fana: At a Speed of Life!

ተመድ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያደርገውንድጋፍ እንዲያጠናክር አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግሥታቱ ድርጅት በድርቅ እና ግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን በመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዴ እና የአካባቢ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን ጋር በተለያዩ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

አቶ ደመቀ ከፊሊፖ ግራንዴ ጋር በነበራቸው ውይይት ኮሚሽኑ በድርቅ እና ግጭት የተፈናቀሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ለመርዳት እያከናወናቸው ላሉ ተግባራት አመስግነው÷ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ፍሊፓ ግራንዴ በበኩላቸው÷ ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት መሥራቱን እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ አቶ ደመቀ መኮንን ከኢንገር አንደርሰን ጋር ኢትዮጵያ እያካሄደችው ባለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር እና በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሠራች መሆኗን ገልፀዋል።

በዚህ ረገድ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግር ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመው÷ መርሐግብሩ ከሀገሪቱ ባሻገር ፋይዳው ለጎረቤት ሀገራት ጭምር መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እምቅ የታደሽ ኃይል ሃብቶቿን በማልማት ምጣኔሃብታዊ እና ማህበራዊ እድገትን ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ተመላክቷል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከታዳሽ የልማት ኘሮጀክቶች አንዱ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ደመቀ÷ ኘሮጀክቱ ከኢትዮጵያ ባሻገር ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።

በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት በንግግር ብቻ የሚፈታ እንደሆነ ጠቅሰው÷ ኢትዮጵያ ሁሌም ለውይይት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

ኢንገር አንደርሰን በበኩላቸው ኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማትን እውን ለማድረግ እያከናወነች ያለውን ተግባር አድንቀው÷ ታዳሽ ኃይል ልማትን ለማስፋፋት የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት የመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ኘሮግራም እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ አለመግባባት በውይይት የሚቋጭበት ሁኔታ መቀጠል እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.