በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የግብርና ዘርፍ ትብብር ላይ የሚመክር መድረክ በቻይና እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት እና በቻይና የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት “በግብርና ትብብር እና በምግብ ምርት ራስን መቻል” በሚል ፅንሰ-ሐሳብ በጥምረት የውይይት መድረክ ማዘጋጀታቸው ተገለጸ፡፡
በውይይት መድረኩ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ፣ የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች እንዲሁም የሮክፌለር ፋውንዴሽን ተወካዮች መገኘታቸው ተጠቁሟል፡፡
ተወያዮቹ በግብርናው ዘርፍ በሚስተዋሉ ፍላጎቶች እና ክፍተቶች ላይ መምከራቸውን በቻይና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስተባበሪያ የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
መድረኩ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በቀጣይ በግብርናው ዘርፍ በምግብ ራሳቸውን ለመቻል ማከናወን በሚገባቸው ጥረት ላይ መምከሩም ተጠቁሟል፡፡