Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት ወደ ሰላም እንዲመጣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አማጺው ቡድን ላይ ጫና መፍጠር ይገባዋል – አምባሳደር ባጫ ደበሌ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ግጭትን ለማስወገድ እና አሸባሪው ህወሓት ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አማጺው ቡድን ላይ ጫና እንዲፈጥር በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ ጥሪ አቀረቡ።

አምባሳደር ባጫ በኬንያ ለተባበሩት መንግስታት ፅህፈት ቤት ሃላፊ ዘይነብ ሃዋ ባንጉራ በፅህፈት ቤቱ ቋሙ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙበትን ደብዳቤ አቅርበዋል።

በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ በተመድ ያላትን ወሳኝ ሚና እና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለፅህፈት ቤት ሃላፊዋ ገለጻ አድርገዋል።

አምባሳደር ባጫ መንግስት ኢትዮጵያ ከተመድ ጋር በአየር ንብረት ለውጥ፣ በከተሞች ልማት እና ዓለም አቀፍ ፀጥታና ደህንነት ያላትን ዘርፈ ብዙ ትብብር አጠናክሮ ለመቀጠል ፅኑ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያ ተመድ በሚያከናውናቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ከፍተኛ ሰራዊት ከሚያሰልፉ አምስት ሀገራት አንዷ ናት ብለዋል።

ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያም ተመድ እና በተለይም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መንግስት እያደረገ ያለውን የሰላም ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ ባለፈም ግጭት ለማስወገድ እና አሸባሪው ህወሓት ወደ ሰላም እንዲመጣ አማጺው ቡድን ላይ ጫና መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

አምባሳደር ባጫ በማብራሪያቸው የኢትዮጵያ መዳከም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት ብሎም ልማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖው የጎላ መሆኑን አስምረውበታል።

በኬንያ የተመድ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሃዋ ባንጉራ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው፥ ተመድ በአፍሪካ ህብረት የቀረበውን የሰላም ሂደት ጨምሮ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፅህፈት ቤቱም የጋራ በሆኑ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ከኤምባሲው ጋር በቅርበት ይሰራል ማለታቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.