ሞዛምቢክና ታንዛኒያ ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሞዛምቢክና ታንዛኒያ ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
የሞዛምቢክና ታንዛኒያ መሪዎች በጋራ ድንበራቸው ላይ ሽብርተኝነትንና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያለመ የመከላከያና የደህንነት ስምምነት ነው የተፈራረሙት፡፡
ሆኖም የተፈረሙት ስምምነቶች ዝርዝር መረጃ ይፋ እንዳልሆነ በዘገባው ተጠቁሟል።
በሀገራቱ ድንበር ከተፈጸሙ ወንጀሎችና የሽብር ተግባራት መካከል ከአምስት ዓመታት በፊት በታንዛኒያ ድንበር አቅራቢያ በሰሜናዊ ሞዛምቢክ በተቀሰቀሰው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡
ሌሎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ከቀያቸው ለመሰደድ የተገደዱበት ሁኔታ ነበር።
የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት ፊሊፔ ኑዩሲ ከዚህ ጋር በተያያዘ በሰጡት አስተያየት ፥ ከአንድ ዓመት በፊት ከአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ የፀጥታ አስከባሪዎች ተሰማርተው አካባቢው ወደቀደመ መደበኛ እንቅስቃሴው እየተመለሰ እንደሆነ ተናግረዋል።
የታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን በበኩላቸው ፥ ሀገራቱ ሀገራት ረጅም ድንበር ስለሚጋሩ ድንበራችንን ለመጠበቅ የሚያስችል አስተማማኝ የደህንነት ስርዓት ያስፈልገናል ነው ያሉት፡፡
በዚሁ ወቅት የሞዛምቢኩ ፕሬዚዳንት በአማጺያን ቁጥጥር ሥር የነበረውን የሞሲምቦ ዳ ፕራያ ወደብና ዋና መሥሪያ ቤት የነበረውን አካባቢ ጎብኝተዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2017 ወደ 30 የሚጠጉ ታጣቂዎች በሞሲምቦ ዳ ፕራያ በሚገኙ ሦስት የፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ወረራ በማካሄድ አመጽ ማስጀመራቸውም ተጠቅሷል፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከ4 ሺህ 258 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፥ ከ820 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው ተሰደዋል፡፡
በሩዋንዳ ወታደሮች የሚደገፈው የሞዛምቢክ ኃይልም በ2021 ወደቡን የተቆጣጠሩትን ታጣቂዎች አስወጥቻለሁ ማለቱን አፍሪካኒውስ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!