Fana: At a Speed of Life!

ሲንቄ ባንክ የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሲንቄ ባንክ የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተገለጸ፡፡

ባንኩ ባዘጋጀው መድረክ አዲሱን ብራንድ በይፋ ማስተዋወቁም ነው የተገለጸው፡፡

በመርሐ-ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ነዋይ መገርሳ፥ ባንኩ ከማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ወደ ባንክ በማደግ ፈር ቀዳጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ባንኩ ዕውን እንዲሆን ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አቶ ነዋይ መገርሳ፥ ባንኩ ከአፍሪካ፣ አዉሮፓና ዩሮ-ኤዥያ አገራት ባንኮች ጋር ለመስራት የሚያስችለውን ዓለም አቀፋዊ ትሥሥር መፍጠሩንም ነው የተናገሩት።

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ቶሎሳ ደገፋ በበኩላቸው ፥ ሲንቄ ባንክ ሲቋቋም ሌሎች የሀገር ውስጥ ባንኮች ሲቋቋሙ ካስመዘገቡት የተከፈለ ካፒታል እጅግ የላቀ ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት 15 ቢሊየን ብር የተመዘገበና 7 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ የሀገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ መቀላቀሉ ፣ ባንኩ አስተማማኝ መሰረት ላይ የተገነባ ተቋም መሆኑን ያመላክታል ብለዋል።

ሰብሳቢው አዲሱ ብራንድ የገዳ ሥርዓት ነጸብራቅ ከሆነው ሲንቄ ባኅረያት የተወሰደ መሆኑንም አብራርተዋል።

የክብር ዶክተር አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉንም የባንኩ አምባሳደር ማድረጉ ነው የተገለጸው።

በመራዖል ከድር

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.