Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ እና ዩክሬን የሰላም ድርድር እንዲያደርጉ ቻይና ጥሪ አቀረበች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ሩሲያ እና ዩክሬን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሰላም ድርድሩን እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ።

ሚኒስትሩ እየተካሄደ ባለው 77ኛው የተመድ ጉባኤ ላይ ትኩረቱን በዩክሬን ላይ ባደረገው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ሀገራቱ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

በዚህ ወቅትም የእያንዳንዱን ሀገር ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መከበር እንዳለበት እና የሁሉም ወገኖች የደህንነት ስጋቶች በትኩረት ሊታይ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ከግጭት መውጫ ብቸኛው መንገድም ውይይት እና ድርድር ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ቻይና ችግሩን ለመፍታት የሚረዱ ሁሉንም ጥረቶች ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗንም ገልፀዋል፡፡

በዚህ ወር ወደ ዩክሬን ዛፖሮዢያ ኒውክሌር ጣቢያ ልዑክ የላከውን የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ሀይል ኤጀንሲ አወንታዊ ሚና ያወደሱት ሚኒስትሩ የኒውክሌር ተቋማት ደህንነትን በተመለከተ ለሙከራ እና ለስህተት ምንም ቦታ የለም ብለዋል፡፡

በፈረንጆቹ መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ በኢስታንቡል ከተደረገው ውይይት በኋላ ሁለቱ ሀገራት ወደ ድርድር ጠረጴዛ አልተመለሱም።

ባለፈው ሳምንት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ ግጭቱን በተቻለ ፍጥነት ለማስቆም ዝግጁ መሆኗን በመጥቀስ ዩክሬን ለሰላም ድርድሩ ፈቃደኛ አይደለችም ማለታቸውን አር ቲ በዘገባው አስታውሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.