Fana: At a Speed of Life!

ዓለም ላይ ከ50 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ለከፋ የረሃብ አደጋ ተጋላጭ ናቸው ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 50 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የከፋ ረሃብ አደጋ አፋፍ ላይ መሆናቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሊ ÷ በአሁኑ ወቅት የረሃብ አደጋ በበርካታ ሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን በር እያንኳኳ ነው ብለዋል፡፡

ኮቪድ-19፣ የሩሲያ- ዩክሬን እና ሌሎች ግግጭቶች፣ የዓየር ንብረት ለውጥ፣ የነዳጅ ዋጋ፣ የአፈር ማዳበሪያ እና የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች ዋጋ መናር ለችግሩ በዋና መንስኤነት እንደሚጠቀሱም አብራርተዋል፡፡

ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበ የመጣው የረሃብ አደጋም ተጋላጭ ዜጎች ህወታቸውን በሰቀቀን እንዲመሩ ካማደረግ ባለፈ በሀገራት ላይ አለመረጋጋት እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ከተጠቀሰው ቁጥር የላቀ ቁጥር ያላቸው የዓለማችን ነዋሪዎች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ለከፋ ረሃብና የምግብ እጥረት ስጋት ውስጥ ገብተዋል።

ለዚህ ችግር የተጋለጡት ሰዎች በ45 ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፥ ለጉዳዩ አስቸኳይ መፍትሄ ካልተሰጠው የከፋ ረሃብና ሰቆቃ ከዚህ ባለፈም አለመረጋጋትን ያስከትላል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

በተጨማሪም በቀጣዩ የፈረንጆች አመት የከፋ የምግብ አቅርቦት ችግር የምድራችን ትልቁ ችግር ይሆናልም ነው ያሉት።

ሀገራት ችግሩን በትብብር እና በቅንጀት የማይፈቱ ከሆነም በቀጣይ ከፍተኛ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል ነው ያመላከቱት፡፡

ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች እና የሰብዓዊ እርዳታ ተቋማትም አስከፊ የረሃብ አደጋ ለተጋረጠባቸው ዜጎች አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ትኩረቱን የምግብ እጥረትና ለርሃብ ምላሽ መስጠት ላይ የሚሰራው “አክሽን አጌንስት ሃንገር” ያወጣው መረጃ ደግሞ ዓለም ላይ 10 በመቶ ሰዎች “የረሃብ ተጋላጭ” መሆናቸውን ያመላክታል።

እንደ መረጃው እነዚህ ሰዎች የሰው ልጅ በቀን መውሰድ ከሚገባው ንጥረ ምግብ መጠን በእጅጉ ያነሰ የሚመገቡ ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.