ግሎባል ፈንድ ኤች አይ ቪን፣ ሳንባ ነቀርሳንና ወባን ለመዋጋት ከ14 ቢሊየን ዶላር በላይ አሰባሰበ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ግሎባል ፈንድ ኤች አይ ቪ፣ ሳንባ ነቀርሳን እና ወባን ለማጥፋት 14 ነጥብ 25 ቢሊየን ዶላር በላይ ማሰባሰቡን አስታወቀ፡፡
ገቢው ከእስካሁኑ ለባለብዙ ወገን የጤና ድርጅት ቃል ከተገባው እንደሚልቅም ነው የተነገረው፡፡
ሆኖም ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረውን 18 ቢሊየን ዶላር ብሪታኒያ እና ጣሊያን ድጋፍ ለማድረግ ባላማሳወቃቸው ዕቅዱ አለመሳካቱ ተገልጿል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሰባተኛው የማህበረሰብ ጤና አጋርነት ጉባዔ ላይ ከአሜሪካ ፣ ጃፓን ፣ ጀርመን ፣ ካናዳ እና አውሮፓ ህብረት መሪዎች ጋር በመሆን የተለያዩ በሽታዎችን ለመዋጋት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አደገኛ የሚባሉ ወረርሽኞችን በመዋጋት ብዙ ድል ተቀዳጅተናል ያሉት ማክሮን ፥ ሆኖም ገና ብዙ ይቀረናል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 38 ነጥብ 4 ሚሊየን ሰዎች ከኤች አይ ቪ (ኤድስ)፣ ሳንባ ነቀርሳ እና ወባ ጋር ይኖራሉ ያሉት ፕሬዚዳንቱ ፥ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በላቲን አሜሪካ የወባና የሳንባ ነቀርሳ በሽታዎች ስርጭት እየጨመሩ በመሆናቸው መዋጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኤች አይ ቪ፣ ወባ እና ሳንባ ነቀርሳ መጥፋት ስላለባቸውና ለ2030 የተገባው ቃል ተፈፃሚ እንዲሆን በቀጣዮቹ ዓመታት ብዙ መሥራት እንደሚገባ መግለፃቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በቀጣዮቹ ሶስት አመታት በዓለም አቀፉ የመድሃኒት መግዣ ድርጅት በኩል 250 ሚሊየን ዩሮ በመመደብ “የመድሃኒት ዋጋን ለመቀነስ የምናደርገውን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉም ቃል ገብተዋል።
ግሎባል ፈንድ በፈርነጆቹ 2002 ከተቋቋመ ወዲህ የ50 ሚሊየን ሰዎችን ህይወት መታደጉም ነው የተገለጸው፡፡
ድጋፍ በሚደረግባቸው ሀገራትም በኤች አይ ቪ፣ ሳንባ ነቀርሳና ወባ የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከግማሽ በላይ ቀንሷል ተብሏል፡፡
የሳንባ ነቀርሳ ሞት 21 በመቶ ሲቀንስ የወባ በሽታ ደግሞ 26 በመቶ ለመቀነስ መቻሉም ነው የተመላከተው።