Fana: At a Speed of Life!

ፀደይ ባንክ ሥራውን በይፋ ጀመረ

 

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞው የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) የአሁኑ ፀደይ ባንክ በይፋ በዛሬው ዕለት ሥራውን ጀምሯል።

 

ባንኩ በ8 ቢሊየን ብር የተከፈለ ካፒታል በ148 ቅርንጫፎች በዛሬው ዕለት በመላ ሀገሪቱ ወደ ሥራ ገብቷል።

 

አብቁተ ወደ ፀደይ ባንክ የተቀየረው የነበሩትን 471 ቅርንጫፎችን ይዞ ነው።
46 ቢሊየን ብር የሚገመት ሀብት ያለው ፀደይ ባንክ ቁጠባ እና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት እንዲሁም የሴቶችን እና የወጣቶችን ተሳትፎ በማሳደግ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተገልጿል።

 

የፀደይ ባንክ ኮርፖሬት ሀብት ዋና ኃላፊ ጋሻው ወርቅነህ ባንኩ አማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በሚል ስያሜ በፋይናንስ ሥራ ውስጥ እያለ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ደግሞ በስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ እንደነበር ጠቅሰዋል።

 

ወደ ባንክነት ደረጃ ከተሸጋገረ በኋላም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።

 

ይህን ለማሳካትም ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት የበለጠ በማጠናከር እና ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን በመጨመር ወደ ሥራ ገብቷል ነው ያሉት።

 

ፀደይ ባንክ ጠንካራ የሰው ኃይል እና ከፍተኛ ሀብት ይዞ ወደ ባንክ ኢንዱስትሪው የገባ በመኾኑ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ነው የተገለጸው።

 

የፀደይ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባደረጉት ንግግር፥ አብቁተ ወደ ፀደይ ባንክ ሲሸጋገር ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረውን የብድርና ቁጠባ አገልግሎት አቋርጦ ሳይሆን በተሻለ ሁኔታ እና በዘመነ አሰራር ይቀጥላል ብለዋል፡፡

 

ባንኩ ሰርተው ማደግን ተሞክሮ ያደረጉ በስራ የሚያምኑ እና በስራ ያስመሰከሩ ብዙሃን ሀብት ነው ያሉት አቶ ገዱ ባንኩ ውጤቱም ቱርፋቱም ህዝባዊ መሆኑን አንስተዋል፡፡

 

የብሄራዊ ባንክ ዋና ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው፥ ፀደይ ባንክ ብድር እና ቁጠባ ተቋም በነበረበት ጊዜ በኢትዮጵያ ከተቋቋሙ የብድር እና ቁጠባ ተቋሞች ቁጥር አንድ የሚባል እንደነበር አስታውሰዋል።

 

ባንኩ አዳዲስ ከተመሰረቱ ባንኮች በተለየ ሁኔታ ወደ ከፍታ እንዲሸጋገር ሊያግዙ የሚችሉ መነሻዎች እንዳሉት በመጥቀስም፥ ለዚህም 12 ሚሊየን ቆጣቢ ደንበኞችን ይዞ ወደ ስራ መግባቱ ትልቅ ማሳያ መሆኑን አውስተዋል፡፡

 

ፀደይ ባንክ በ1988 ዓ.ም “የገጠር ብድር አገልግሎት” በሚል ሥራ የጀመረ ሲሆን፥ በ1989 ዓ.ም አብቁተ የሚለውን ስያሜ በመያዝ በአማራ ክልል በ10 ዞኖች ወደ ማይክሮፋይናንስ ተቋም በማደግ ሲሰራ ቆይቷል።

 

በወቅቱም በ3 ሚሊየን ብር ካፒታል ተነስቶ ዛሬ ጠቅላላ ሃብቱ 45 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የደረሰ ሲሆን፥ የተጣራ ካፒታሉ 11 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ደርሷል ነው የተባለው።

 

አሁን ላይ የፀደይ ባንክ የተፈረመ ካፒታል 7 ነጥብ 75 ቢሊየን ብር ሲሆን፥ የ10 ሺህ ብር ዋጋ ያላቸው 774 ሺህ 907 አክሲዮኖች አሉት።

 

በሥራ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.