Fana: At a Speed of Life!

የአሸባሪዎች ጥቃት የኢትዮጵያን ብልጽግና ከማረጋገጥ አያስቆመንም- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

 

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሸባሪዎች የጥፋት እርምጃ ጥቃት የኢትዮጵያን ብልጽግና ከማረጋገጥ ለማስቆም እንደማይችል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

 

አገልግሎቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ ከሰሞኑ አሸባሪው ሸኔ ሆሮጉድሩ ወለጋ በንጹሐንና ዜጎችና በአካባቢው ሚሊሻ አባላት ላይ ግድያ መፈጸሙን አስታውሷል።

 

በተለያዩ የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በጸጥታ ኃይሎችና በሕዝቡ ቅንጅት እርምጃ የተወሰደበት ይህ አሸባሪ ቡድን እየተበተነ ወደ ሆሮ ጉድሩ ጃርደጋ ጃርቴ አካባቢ ሲሸሽ እንደነበርም አመላክቷል።

 

አሸባሪው ሸኔ ይህን ግድያ በንጹሐን ላይ የፈጸመው በትናንትናው ዕለት የተደመሰሰበትን ጃል ኡርጂ የተባለውን የአካባቢውን የሸኔ አዛዥ እና ጀሌዎቹን ደም ለመበቀል እና የመስቀልና የኢሬቻን በዓላትን ከወዲሁ ለማወክ በማሰብ መሆኑንም መግለጫው ጠቅሷል።

 

በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው አካባቢውን ከአሸባሪው ሸኔ በማፅዳት ላይ እንደሚገኙም አስታውቋል።

 

“ታሪካዊ ጠላቶቻችን በተለያዩ ቦታዎች ዓላማቸው ሲሰናከልባቸው በንጹሐን ላይ የሚፈጽሙት የጭካኔ ድርጊት እጅግ አሳዛኝ” መሆኑንም መግለጫው አውስቷል።

 

“ሆኖም ይህ የአሸባሪዎች የጥፋት እርምጃ የኢትዮጵያን ብልጽግና ከማረጋገጥ ሊያስቆመን አይችልም” ብሏል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.