Fana: At a Speed of Life!

የብድር እና ቁጠባ ተቋማት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው – ዶክተር ይናገር ደሴ

 

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብድር እና ቁጠባ ተቋማት በሀገራችን የልማት እንቅስቃሴ በተለይም አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ገለጹ፡፡

 

ዶክተር ይናገር ደሴ ፀደይ ባንክ ብድር እና ተቋም በነበረበት ጊዜ በሀገራችን ከተቋቋሙ የብድር እና ቁጠባ ተቋሞች ቁጥር አንድ የሚባል ነበር ብለዋል፡፡

 

ባንኩ አዳዲስ ከተመሰረቱ ባንኮች በተለየ ሁኔታ ወደ ከፍታ እንዲሸጋገር ሊያግዙ የሚችሉ መነሻዎች አሉት ያሉት ዶክተር ይናገር፥ ለዚህም 12 ሚሊየን ቆጣቢ ደንበኞችን ይዞ ወደ ስራ መግባቱ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

 

አጠቃላይ የኢትዮጵያ ባንኮች 330 ሺህ የባንክ ብድር ደንበኛ እንዳላቸው ጠቁመው፥ የብድር እና ተቋማት የብድር ደንበኞች ግን ወደ 6 ሚሊየን እንደሚጠጋ አመላክተዋል።

 

ከዚህ አንጻርም ለአብዛኛው ህዝብ የብድር አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት እነዚህ ተቋማት ናቸው ብለዋል፡፡

 

በዚህ ሂደት ውስጥ የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም በአማራ ክልልም ይሁን በሌሎች ክልሎች ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷልም ነው ያሉት።

 

ዘመኑ ከሚጠይቀው የባንክ አገልግሎት አኳያ ፀደይ ባንክ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ዘመኑን የሚመጥን አሰራረሮችን መዘርጋት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

 

የፀደይ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ÷በምስረታው ተገኝተው እንዳሉት አብቁተ ወደ ፀደይ ባንክ ሲሸጋገር ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረውን የብድርና ቁጠባ አገልግሎት የአቋርጦ ሳይሆን በተሻለ ሁኔታ እና በዘመነ አሰራር ለመቀጠል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 

ፀደይ ባንክ ሰርተው ማደግን ተሞክሮ ያደረጉ በስራ የሚያምኑ እና በስራ ያስመሰከሩ ብዙሃን ሀብት ነው ያሉት አቶ ገዱ ባንኩ ውጤቱም ቱርፋቱም ህዝባዊ መሆኑን አንስተዋል፡፡

 

በአመለወርቅ ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.