አቶ ርስቱ ይርዳው በሜሪጆይ ኢትዮጵያ ለሚገኙ አረጋውያን ማዕድ አጋሩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ በሜሪጆይ ኢትዮጵያ ሐዋሳ ቅርንጫፍ ለሚገኙ አረጋውያን ማዕድ አጋሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት ፥ በእድሜ የገፉ አረጋውያንን መደገፍ ከሁሉም አካላት ይጠበቃል ብለዋል።
በሀገር እድገት የአረጋውያን አሻራ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ ከእነርሱ መልካምነትን መከባበርንና ፍቅርን ተምረናል ነው ያሉት።
በመሆኑም አባቶቻችንና እናቶቻችንን መንከባከብ ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።
ሀገር የምትገነባው በቅብብሎሽ መሆኑን ገልጸውም ፥ አረጋውያንን በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
በማህበረሰብ ዛሬ የሚከበረው የእናቶች የመስቀል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ ቀኑን ምክንያት በማድረግ ለሀገር ባለውለታዎች ማዕድ ማጋራት አስፈላጊ ሆኖ ማግኘታቸውን አንስተዋል።
የመስቀል በዓል እንደደቡብ ክልል አንድም ለክርስትና እምነት ተከታዮች ሀይማኖታዊ በዓል ሲሆን ፥ በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች የዘመን መለወጫ በዓል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመስቀልን በዓልም በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ምክንያትመሆኑንም ጠቁመዋል ።
ከርዕሰ መስተዳድሩ ድጋፍ በተጨማሪ የክልሉ መንግስት ለአረጋውያን ማዕከሉ የ300 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል።
የሜሪጆይ ማዕከልን በመመስረት አረጋውያንን ላሰባሰቡ ለሲስተር ዘቢደርና ለስራ ባልደረቦቻቸው ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል።
የሜሪጆይ ኢትዮጵያ ሐዋሳ ቅርንጫፍ የፕሮግራም ማናጀር አቶ እስክንድር ሽመልስ እንደገለጹት ፥ በርዕሰ መስተዳድሩ የግል ተነሳሽነት ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የሀገር ባለውለታ የሆኑ አረጋውያንን መደገፋቸው በሌሎችም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ዘንድ የሚፈጥረው ተነሳሽነት በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!