“ዮ…ማስቃላ” በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋሞ የዘመን መለወጫ በዓል “ዮ…ማስቃላ” በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ነው፡፡
በዓሉ በጋሞ ዞን አስተዳደር ግቢ ውስጥ የተገነባውና የጋሞ ብሔር የሰላም ተምሳሌት ምልክት በሆነው ሐውልት ምረቃ ተጀምሯል።
በበዓሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዎች አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እና አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ታድመዋል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ በጋሞ ዞን ባህል ማዕከል የተዘጋጀ ዓውደ ርዕይ በበዓሉ ታዳሚዎች ተጎብኝተዋል።
በዓውደ ርዕዩ የጋሞ የጥበብ ሥራዎች እንዲሁም ማህበረሰቡ በደስታና በሀዘን ጊዜ የሚጠቀምባቸው ባህላዊ ቁሶች ለዕይታ ቀርበዋል።
በቀጣይም “ ዮ… ማስቃላ በዓልን አስመልክቶ በተካሄዱ ጥናታዊ ጽሁፎች ላይ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በክብረ በዓሉ እና በቢዝነስ ፎረሙ ላይ ለመሳተፍ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብን ጨምሮ የተለያዩ ባለሀብቶችም አርባምንጭ ከተማ መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል።
በተጨማሪም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ሀደ ስንቄዎች፣ የጥበብ ባለሙዎችና ተጋባዥ እንግዶች መገኘታቸውም ነው የተገለጸው፡፡