Fana: At a Speed of Life!

ፖሊስ በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የደመራና የመስቀል በዓላት በሰላም እንዲከበሩ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ፡፡

ለደመራና መስቀል በዓላት ዝግ የሚሆኑ መንገዶችንም ፖሊስ  ይፋ አድርጓል፡፡

ሰኞ መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም የእምነቱ ተከታዮች፣ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ  ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሚገኙበት የደመራ በዓል ሥነ-ሥርዓት በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድ ተጠቅሷል፡፡

የበዓሉን አከባበር  በተመለከተ ጉዳዩ በቅርበት ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ኃላፊዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነውም ተብሏል፡፡

በከተማ ደረጃ የደመራ ስነ-ሰርዓት ወደ ሚከናወንበት መስቀል አደባባይ ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ ስፍራዎች  የጦር መሳሪያ ፣ ስለታም ነገሮችን እና ህገወጥ ቁሳቁሶችን ይዞ መምጣት የተከለከ  እና ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ እንደሚኖር ህብረተሰቡ ተገንዝቦ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በመስቀል አደባባይ የሚካሄደው የደመራ ፕሮግራምን መጠናቀቅ ተከትሎ በከተማዋ በተለያዩ ደብሮች እና  መንደሮች ደመራ የማብራት ስነ-ስርዓት ይካሄዳልም ነው የተባለው፡፡

በየአካባቢው ደመራ ሲበራ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደረግ እንደሚገባ እና በማንኛውም ሁኔታ ርችት መተኮስ ፍፁም ክልክል መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡

በመስቀል አደባባይ የደመራ  ሥነ-ሥርዓት ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ዝግ የሆኑ መንገዶችንም ይፋ አድርጓል፡፡

በዚሁ መሰረት፡-

  • ከመገናኛ ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከኤድናሞል በአትላሳ ወደ ካዛንቺስ የሚወስደው መንገድ  ኡራኤል አደባባይ
  • ከጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ አጎና ሲኒማ
  • ከጎፋ በአዲሱ መንገድ ወደ ለገሃር ለሚመጡ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን መስቀለኛ ላይ
  • ከቡልጋሪያ በሜክሲኮ አደባባይ ወደ ለገሃር የሚሄዱ ጠማማ ፎቅ አካባቢ
  • ከሳር ቤት ወደ ሜክሲኮ አደባባይ እንዲሁም ከጦር ኃይሎች በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወደ ለገሃር የሚወስደው ሚክሲኮ አደባባይ
  • ከተከለ ሃይማኖት በጎማ ቁጠባ ወደ ለገሃር ሰንጋተራ 40/60 ኮንደሚኒዬም አካባቢ
  • ከጌጃ ሰፈር ፣ በአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚሄዱ አሽከርካሪዎች ጎማ ቁጠባ
  • ከመርካቶ በተክለ ሃይማኖት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሜትሮሎጂ በር ላይ
  • ከራስ ቴአትር በጎላ ሚካኤል ውስጥ ለውስጥ ጎላ ሚካኤል መስቀለኛ
  • ከተክለ ሃይማኖት ጥቁር አንበሳ ኢሚግሬሽን ጥቁር አንበሳ ሼል
  • ከፒያሳ በቸርችር ጎዳና ለገሃር ቴዎድሮስ አደባባይ
  • በአሮጌው ቄራ ፍል ውሃ ንግድ ማተሚያ ቤት
  • ከካዛቺስ ወደ ሂልተን ካዛንቺስ ቶታል
  • ከአዋሬ በካዛንቺስ ወደ ፍል ውሃ የሚወስደው መንገድ የቀድሞ 6ኛ ፖሊስ መታጠፊያ ላይ ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ ዝግጅቱ እስከሚጠናቀቅ ድርስ ለተሽከርካሪዎች ዝግ እንሚደረግ አስታውቋል።

ህብረተሰቡም ይህንኑ  አውቆ አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀም እና በተገለፁት መንገዶች ላይ ለአጭርም ሆን ለረጅም ሰዓት ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ፍፁም ክልክል መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ህብረተሰቡ የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት መረጃ ለመስጠት 991 ወይም 816 ነፃ የስልክ መስመሮችን እና 01- 11 -11- 01 -11፣ 01- 11- 26- 43- 59 እና 01- 11- 01- 02- 97፣ መጠቀም የሚችል መሆኑን ተገልጿል፡፡

ለስራው ስኬታማነት ህብረተሰቡ እያደረገ ላለው ትብብር  የአዲስ አበባ ፖሊስ  ምስጋና ያቀረበ ሲሆን፥  ለመላው የእምነቱ ተከታዮች በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆንላቸውም መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.