Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት ለአፍሪካ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግሥታቱ ድርጅት ለአፍሪካ ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለበት የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኒውዮርክ ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የመንግሥታቱ ድርጅት 77ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እያካሄደች ያለው ጥረትና በአረንጓዳ ዐሻራ መርሐ ግብር እያስመዘገበች ያለው ውጤት ዓለም አቀፍ እውቅና እና ድጋፍ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት በቂ ቦታ ሊሰጣትና ትክክለኛው የአፍሪካ ድምጽ ሊሰማ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።

ሰብዓዊ መብትን የፖለቲካ ዓላማ ማራመጃ መሳሪያ አድርጎ የመጠቀም ተግባር ሊቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ለአገራቸው ብልጽግና የሚሰሩ የአፍሪካ መንግሥታት ተገቢው ድጋፍ ሊደርግላቸው እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በንግግራቸው።

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሆኑ በካይ ጋዝ ልቀት ያላት ድርሻ ከቁጥር የማይገባ ቢሆንም ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዞችን ለመቀነስ ግን የተለያዩ ስራዎችን እየከወነች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ እየተገበረችው ባለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በበርካታ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች መተከላቸውን ያነሱት አቶ ደመቀ፥ አሁን ላይ ጠንካራ የደን ተከላ ባህል ማዳበር መቻሉን ተናግረዋል ።

ኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው የኢነርጂ ሽግግር እና የአረንጓዴ እድገት እያስመዘገበች ነው ብለዋል። ይህ ተግባሯም እውቅና እና ተግባራዊ ድጋፍ ሊቸረው ይገባል ብለዋል።

በሌላ በኩልም አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የጠየቁ ሲሆን፥ አፍሪካውያን ጥያቄያችን ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ሁልጊዜም ይህን ጥያቄ አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።

የአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን የሚችለው በፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ተገቢው ውክልና ሲኖራት መሆኑንም አስረድተዋል ።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በማኅበራዊ ፣ በኢኮኖሚ እና በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለውጥ ማሳየቷን የተናገሩት አቶ ደመቀ ፥ እንደ አገር ህልውናዋን የሚፈታተኑ ችግሮችም እንዳጋጠሟት ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የህወሓት ቡድን እ.ኤ.አ በህዳር 2020 ላይ በሰሜን ዕዝ ላይ የከፈተውን ጥቃት ተከትለው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራች መሆኑን አንስተዋል ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ግጭት በአፍሪካ ህብረት አማካይነት በሚደረግ የሰላም ድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

ከአፍሪካ ሕብረት ውጭ የሚደረግ ሌላ አካሄድ ተቀባይነት አይኖረውም ብለዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር በሚደረግ የሦስትዮሽ ድርድር ጉልሕ ተፅዕኖ በማያደርስ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህን መሰረት በማድረግ ልዩነቶችን ለመፍታት አሁንም ፅኑ አቋም አላት ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.