የደመራ በዓል ሲከበር የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲደረግ ኮሚሽኑ አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኀብረተሰቡ የመስቀል ደመራ በዓልን ሲያከብር ድንገተኛ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡
በዓሉን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የከተማ አስተዳደሩ እሳትና ድንገተኛ አደጋ ቁጥጥር ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ፥ የደመራ እና የመስቀል በዓል በሰላም እና በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር ከተማ አስተዳደሩ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በነገው እለትም የሃይማኖት አባቶች የሚሳተፉበት የጽዳት ዘመቻ እንደሚካሄድ ጠቅሰው፥ ውሃን ጨምሮ አስፈላጊ አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆኑ በቅንጅት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
በበዓሉ ወቅት የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ኀብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው ናቸው፡፡
ኀብረተሰቡ ደመራ በሚለኩስበት ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ኮሚሽኑ ለድንገተኛ እሳት አደጋ ቁጥጥር አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓልም ነው ያሉት፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስርጭት የቴክኒክ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ በበኩላቸው፥ የደመራ ቦታዎች ከኤሌክትሪክ መስመሮች ቢያንስ 20 ሜትር መራቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ለበዓሉ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ችግር እንዳያጋጥም ዝግጅት መደረጉን መግለጻቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
በደመራ አከባበር ወቅት ድንገተኛ የእሳት አደጋ ቢከሰት በነጻ የስልክ መስመር 939 በመደወል ማሳወቅ እንደሚገባም መልዕክት ተላልፏል፡፡