Fana: At a Speed of Life!

የማሕፀን በር ካንሰር- አምጪ ቫይረስ መከላከያ ክትባት ላይ ያተኮረ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የማሕፀን በር ካንሰር አምጪ ቫይረስ መከላከያ ክትባት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የዘርፉ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲምፖዚየሙ÷ የማሕፀን በር ካንሰር- አምጪ ቫይረስ መከላከያ ክትባትን በተመለከተ የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት መድረክ ነው ተብሏል።

በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ÷ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ የማሕፀን በር ካንሰር ክትባት መስጠት መጀመሯን ገልጸዋል፡፡

ከአፍሪካ አበረታች ውጤት ካስመዘገቡ አራት ሀገራት አንዷ መሆን እንደቻለችም ጠቅሰዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በትምህርት ቤቶች በመጀመሪያው ዶዝ 4 ነጥብ 8 ሚሊየን እና በሁለተኛው ዶዝ 3 ነጥብ 1 ሚሊየን የሚሆኑ ልጃገረዶች ክትባቱን እንዲያገኙ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

በማሕፀን በር ካንሰር ምክንያት የሚመጣውን ሞት ለመቀነስ የተጀመረው የተቀናጀ ሃገራዊ ቫይረሱን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚኒስትር ዴኤታው መግለጻቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

እንደ አፍሪካም ሆነ እንደ ዓለም ሴቶች በቫይረሱ የማይሞቱበትን ጊዜ ለማምጣት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.