Fana: At a Speed of Life!

ግጭት ቀስቃሽ ጽሑፎችና ሁከት ቀስቃሽ ነገሮችን በዓሉ ወደ ሚከበርበት ቦታ ይዞ መምጣት በጥብቅ የተከለከለ ነው – የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ አጀንዳዎችን ማራገብና ማንፀባረቅ ተገቢ እንዳልሆነ ሁሉም ተገንዝቦ ከበዓሉ ሥነ ስርዓት ውጪ ግጭት ቀስቃሽ ጽሑፎች እና ሁከት ቀስቃሽ ነገሮችን በማንኛውም ሁኔታ በዓሉ ወደ ሚከበርበት ቦታ ይዞ መምጣት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን ግብረ ኃይሉ ገለጸ፡፡

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የደመራ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

ግብረ ኃይሉ በበዓሉ አከባበር ላይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ማካሄዱን ገልቷጿል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ ቤተክርስቲያኗ የ2015 ዓ.ም የደመራ በዓልን ለማክበር ከወቅታዊ ሁኔታ አንጻር እጅግ ጥንቃቄ በማድረግ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት አድርጋለች፡፡

ግብረ ኃይሉ ከቤተክርስቲያኗ ሥርዓት ውጭ የበዓሉን ድባብ ለማደብዘዝ እና ክብሯን ለመንካት በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ሥርዓት እንዲያሲዝ የሃይማኖት አባቶች ጠይቀዋል።

ግብረ ኃይሉም በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከሃይማኖት አባቶችና ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት እና ዝግጁነት ገልጿል።

የአልሸባብ የሽብር ቡድን እንዲሁም ሌሎች ፀረ ሰላም ኃይሎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሽብር አደጋ ለማድረስ ጥረት እያደረጉ መሆኑንና በዓሉ በሰላም እንዳይጠናቀቅ የተለያዩ የግል አጀንዳዎችን አንግበው የበዓሉን ስነ ሥርዓት ለማወክ የተዘጋጁ ኃይሎች እንዳሉ ግብረ ኃይሉ ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡

በመላው ሀገራችን በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በቂ ዝግጅት በማድረግ ስምሪት ወስዶ እየሠራ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

በሽብር ኃይሎች ላይ እየወሰደ ያለውን ጠንካራ እርምጃም አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ግብረ ኃይ ያረጋገጠው፡፡

በሃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ አጀንዳዎችን ማራገብና ማንፀባረቅ ተገቢ እንዳልሆነ ሁሉም ተገንዝቦ ከበዓሉ ሥነ ስርዓት ውጪ ግጭት ቀስቃሽ ጽሑፎች እና ሁከት ቀስቃሽ ነገሮችን በማንኛውም ሁኔታ በዓሉ ወደ ሚከበርበት ቦታ ይዞ መምጣት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን ግብረ ኃይሉ በአጽንኦት ገልጿል፡፡

ይህንን ክልከላ ተላልፈው የበዓሉን ድባብ ለማደብዘዝ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አሳስቧል፡፡

የደመራ በዓል ከሚፈቅደው ስነ ስርዓት ውጪ በበዓሉ ድባብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚደረግ ማንኛውም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ÷ የሃይማኖት አባቶች፣ የየደብሩ አስተዳደሮች፣ በዓሉን በኮሚቴነት የሚያስተባብሩና የሚመሩ አካላት፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲሁም ወጣቶች ከፀጥታ አካላት የሚሰጠውን መመሪያ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲል ግብረ ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የበዓሉ ታዳሚዎች የበዓሉን ሥነ ስርዓት የሚያውክ የተለየ እንቅስቃሴ ሲመለከቱ ለፀጥታ አካላት መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሲል ጠይቋል፡፡

ግብረ ኃይሉ÷ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.