ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2015 ( ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፥ የመስቀል በዓል ያለፈውን ፈተና የምናስወግድበትና ለመጪው ተስፋ የምንሰንቅበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያም በዚህ ዓመት የከረሙ ችግሮቿን እንድትፈታና ገበታዋን ለልጆቿ በሚያስፈልጋቸው ምግብ እንድትሞላ፣ ኢትዮጵያን የምንወድ ሁሉ ቆርጠን እንነሳ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ!
አስቸጋሪው የክረምት ወቅት ወጥቶ፣ የጠራውና አስደሳቹ የመጸው ወቅት በሚጀምርበት ወቅት ላይ እንገኛለን። የሞላው ወንዝ ይጎድላል፤ ፈታኙ ጭቃ ይደርቃል፤ ጥሻው ይገለጣል፤ ጨለማውም ይበራል፤ ብርዱ ይቀልላል፤ ሜዳና ተራራው በአበባ ያጌጣል። በዚህ ወቅት ነው ተሠውሮ የኖረው መስቀል የተገኘበትን በዓል የምናከብረው።
ኢትዮጵያውያን የሚያስተሣሥረን ገመድ ሊበጠስ የማይችል ጠንካራ መሆኑን ከሚያሳዩን ወቅቶች አንዱ ወርሃ መስከረም ነው። አብዛኞቹ የሀገራችን ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላቸውን፣ ወይም ደግሞ የዓመቱን ታላቅ የምስጋና በዓላቸውን የሚያከብሩት በዚህ በመስከረም ወቅት በተቀራራቢ ጊዜ ነው። ይህ እንደ እንግዳ ደራሽ፣ እንደ ውኃ ፈሳሽ በድንገት ወይም በአጋጣሚ የሆነ አይመስልም። መነሻው አንዳች የጋራ ዕሳቤ እንደሚኖረው ይጠቁመናል። መነሻው የአንድነታችን፤ የአከባበሩ ልዩ ልዩ መሆን ደግሞ የኅብራዊነታችን ማሳያ ነው።
በአብዛኛው አከባበራችን ደመራው፣ ችቦው፣ የወጣትና የልጆች ፌሽታ፣ ለሽማግሌዎች የሚሰጠው ቦታ፣ ምርቃቱ፣ መልካም ምኞቱ ተቀራራቢ ነው። ይህ ነገር ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ተመሳስሎና ተቀራርቦ ሲከበር ስናይ፣ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገራችን የተሣሠረችበትን ውስጣዊ ሥር እንድንመረምር ያደርገናል።
ደመራው ሲለኮስ ጨለማው በብርሃን፤ ቁርና ብርዱ በሙቀት፤ ድብርቱ በተስፋ ይተካል። አስቸጋሪውንና ፈታኙን ወቅት መሻገራችንን ደመራው ያበሥራል። ማንም ባይነግረንም የመስኩ አበባና የሰማዩ ጥራት፣ የወፎች ዝማሬና የጅራፉ ጩኸት መስከረም እንደጠባ ይመሰክራል። አበባው ወደ ፍሬ፣ ፍሬው ወደ ምርት የሚሸጋገረው በዚህ ወቅት ነው። በጎመን የከረመ ማጀት በገብስ ገንፎና በልዩ ልዩ እሸት ሰብሎች መሞላት ይጀምራል። ከክረምቱ ጋር አስፈሪ የነበሩት ወንዞች በመስከረሙ ግርማ ጉልበታቸው ላልቶ ዘመዳሞች ለመጠያየቅ፤ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ይሰናዳሉ። ወቅቱ ይዟቸው በሚመጣቸው ክብረ በዓላትና ልዩ ልዩ ሁኔታዎች ምክንያት መስከረም ለኢትዮጵያችን ትልቅ ተምሳሌት ነው።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
በአስቸጋሪና በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ አልፈን እዚህ ደርሰናል። መንገዳችን ጨለማ፣ እግራችን ቄጤማ እንዲሆን ብዙ ተሠርቶብናል። ከድጡ ወደ ማጡ እንድንወርድ ያልተፈተለ ሤራ የለም። እንጀራችንን የበሉ ተረከዛቸውን አንሥተውብናል። ወንዙ እንዲሞላብን፣ ጎርፉ እንዲደርስብን፣ ናዳ እንዲወርድብን ብዙ ተሠርቶ ነበር። የኢትዮጵያ አምላክ ግን አሳልፎ አልሰጠንም።
ስለ ረሃብ እየተነገረብን፣ ምድሪቱ አትረፍርፋ ሰጠችን። ስለ በረሃማነት እየተሟረተብን ሀገራችን አረንጓዴ ለበሰች። ስለ ኪሣራ እየተለፈለፈ፣ ኢኮኖሚያችን ፈተናዎቹን እየተሻገረ ቀጠለ። ከግራ ከቀኝ እየተዋከብን ሦስተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ ሞልተን ተርባይናችንን አስነሣን። እንድንለያይ መዓት እየተወራ፣ የሕዝባችን አንድነት እንደ ብረት ጠነከረ፤ እንደ አልማዝ አበራ። ደክመዋል ተብሎ ሲዘመትብን፣ በጽናት ቆመን አሳየን። የትም አያደርሷቸውም የተባልንባቸው ፕሮጀክቶቻችን በመጠናቀቅ ላይ ናቸው።
ይህ ሁሉ አልሳካ ሲል ደግሞ ትእግሥታችን እንደ ፍርሃት፣ ሰላም ፈላጊነታችን እንደ ድክመት ተቆጥሮ ሦስተኛ ዙር ጥቃት ተፈጸመብን። የታገሥነው በዚህም ሆነ በዚያ ወገን የሚያልቀው የእኛው ሕዝብ ነው ብለን ነው። እነሱ ሲከፉ እኛ የለዘብነው፣ የአንድ ሀገር መንግሥትና የአንድ ሀገር ዐመጸኛ እኩል ለሕዝብ አያስቡም ብለን ነው። ከጸብ ይልቅ ፍቅር ይሻላል ስንል ምላሹ እብሪት እየሆነብን ጭምር በንግግር ፋንታ ኃይል የመጠቀም ፍላጎት አላደረብንም። ከጦርነት በላይ ከሰላም እናተርፋለን ብለን እየተወጋንም ቢሆን የሰላም እጆችን ከመዘርጋት አልተቆጠብንም። ሰላም ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ አይመጣም።
በዚህ የተነሣ ሀገራዊ ሕልውናችንን ለማስጠበቅ ስንል ወደ መከላከል እንድንገባ ተገድደናል። የዛሬው ብቻ ሳይሆን የመጭውም ትውልድ አደራ አለብን። ኢትዮጵያን ከመጥፋት ለመታደግ፣ ሕዝብን ከብተና ለማዳን እና ሀገር እንደ ሀገር ቀጥላ የልጅ ልጆቻችን ሉአላዊት ኢትዮጵያን እንዲወርሱ ስንል የመጨረሻውን የመከላከል አማራጭ ወስደናል። አሁንም እያደረግን ያለነው የመከላከል ውጊያ ይኼንን ታሪካዊ አደራ ለመወጣትና ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ከአደጋ ለመከላከል ያሰበ ነው።
ለኢትዮጵያ መንግሥት ስለ ሰላም ማስተማር ማለት ለዓሣ ዋናን ለወፍ መብረርን ማስተማር ነው። ‹ሰላም› ራሷ የኢትዮጵያ መንግሥት የከፈለላትን ዋጋ ያህል የከፈለላት የለም። የገጠመን ወረራ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከሚፈለግብን በላይ አድርገናል። የእኛን ጥረት በተገቢ መንገድ የሚያወድስና የሌላኛው ወገን እምቢታ በተገቢው ልክ የሚያወግዝ ግን ጥቂት ነው። ለሰላም የተዘረጉ እጆች ሰላምን የሚመርጡት፣ ጦር ለመያዝ ስለማይችሉ አይደለም፤ ሰላምን ስለሚመርጡ ብቻ ነው። ለሰላም የዘረጋነው እጅ ምንም ዋጋ ስላላገኘ ጦር እንዲይዝ እየተገደደ ነው።
በተለያዩ አካባቢዎች፣ በከተማና በገጠር፣ በአርሶና በአርብቶ አደር መንደሮች፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር፣ በመሐልና በግንባር ሆናችሁ የብርሃነ መስቀሉን በዓል ለምታከብሩ ሁሉ፤ አንድ ነገር ላረጋግጥላቸሁ እወዳለሁ። ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት በሁለት እጆቿ እየሠራች ፈተናዋን ትሻገረዋለች። በአንድ እጇ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚገባ አስጠብቃ ችግሯን ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ትታገላለች። በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝባችን በወዙ ጎተራው እንዲሞላ፤ ምሳውን በብድር ሳይሆን ከራሱ ማሳ ዘግኖ እንዲመገብ የሚችልበትን ስትራቴጂ ነድፈን መንቀሳቀስ እንጀምራለን።
ይህ ጉዞአችን “የሌማት ትሩፋት” ይባላል። ዓላማው በቀላል መንገድ ገበታችንን በተመጣጠነ ምግብ መሙላት ነው። የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቀላል የዶሮ ርባታ፣ ቀላል የወተት ላሞች ርባታና የዓሣ ርባታን ይይዛል። አሁን ያለንበት ዘመን በአነስተኛ ቦታዎች፣ ቀላል ቴክሎጂዎችን በመጠቀም፣ በምግብ ራሳችን ለመቻል የሚያስችሉ ዕድሎች የተፈጠሩበት ዘመን ነው። ታላላቅ የእርሻ መሬት የሌላቸው ሀገሮች ይሄን መንገድ ውጤታማ ሆነውበታል። አረንጓዴ ዐሻራን ውጤታማ እንዳደረግነው ሁሉ፣ ወገባችንን አሥረንና እጅጌያችንን ሰብስበን ጎተራና ማጀታችን እንዲሟላ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ታጥቀን እንሠራለን።
የመስቀል በዓል ያለፈውን ፈተና የምናስወግድበትና ለመጪው ተስፋ የምንሰንቅበት ነው። የአከባበሩ ሥነ ሥርዓትና የሽማግሌዎች ምርቃት ይሄንን ያሳየናል። ኢትዮጵያም በዚህ ዓመት የከረሙ ችግሮቿን እንድትፈታና ገበታዋን ለልጆቿ በሚያስፈልጋቸው ምግብ እንድትሞላ፣ ኢትዮጵያን የምንወድ ሁሉ ቆርጠን እንድንነሣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ።
በድጋሚ እንኳን ለመስቀል በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መስከረም 16፣ 2015 ዓ.ም