የሐረሪ ክልል ህዝበ ክርስቲያኑ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባህሉን በመተግበር በዓሉን እንዲያከብር ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 16 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለደመራና ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ እያለ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፈ።
የመስቀል በዓል ለረጅም ጊዜ የተራራቁ የቤተሰብ አባላት እና ወዳጅ ዘመዳሞች የሚገናኙበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተቸገሩ ወገኖች የሚደገፉበት፣ አዲስ ጎጆ የሚመሰረትበት እና ሌሎች ማህበራዊ ኩነቶች የሚከወኑበት ታላቅ በዓልም ነው ብሏል በመልዕክቱ።
በርካታ ህዝብ በታደመበት የሚከበረው የደመራ በዓል አከባበር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርትና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) መመዝገቡን አስታውሷል።
ህዝበ ክርስትያኑ የደመራ በዓል አከባበር እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር በማድረግ የተቸገሩ ወገኖችን በማብላትና የተጠሙትን በማጠጣት እንዲሁም የተለመደ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባህሉን በመተግበር በዓሉን እንዲያከብር ጥሪውን አቅርቧል።
በተያያዘም ህዝበ ክርስትያኑን ጨምሮ መላው የክልሉ ነዋሪ ሰላምን፣ አብሮነትን፣ መተባበርንና ወንድማማችነት በማጎልበት እንዲሁም በክልሉ የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ የልማት ተግባራት እንዲጠናከሩ ድጋፋን እንዲያጠናክርም መልዕክት አስተላልፏል።
በዓሉም የሰላም፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የደስታና የፍቅር እንዲሆን ከልብ ይመኛል።