Fana: At a Speed of Life!

ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው÷ህዝበ ክርስቲያኑ የመስቀል በዓልን ሲያከብር እሴቱን በጠበቀ መልኩ የተቸገሩ ወገኖችን በማብላትና የተጠሙትን በማጠጣት ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል።

ህብረተሰቡ የተለመደ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባህሉንም በመተግበር በዓሉን ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እንዲያከብርም ጥሪ አቅርበዋል።

የተጀመረው የእድገት እና የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን በየአካባቢያችን ሰላማችንን አጽንተን ያሉንን ጸጋዎች በመጠቀም ሙሉ አቅማችንን እና ትኩረታችንን በልማት ላይ ልናደርግ ይገባል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

መስቀል በሁሉም አካባቢዎች የሰላም፣ የአብሮነት፣ የመተሳሰብ፣ የመደጋገፍ፣ የመከባበር እንዲሁም የተጣሉ ይቅር የሚባባሉበት እሴቶች ደምቆ የሚታይበት በዓል እንደሆነም አውስተዋል።

ህዝቡ ከሁሉም በላይ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ጀግኖችን በማሰብ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

የመስቀል በዓል ለክልሉ ህዝብና ለመላው ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የመተሳሰብ እንዲሆንም ተመኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.