Fana: At a Speed of Life!

አገልግሎቱ በህገ-ወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በህገ-ወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የኢፌዴሪ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አሳሰበ፡፡

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷አንዳንድ አካላት በህጋዊ የገንዘብ ማስተላለፍ (ህጋዊ ሐዋላ) ሽፋን ገንዘብ የማስተላለፍ ድርጊት እየፈጸሙ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ ከተለያዩ ምንጮች ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ማሳጣት ብሎም የውጭ ምንዛሪውን በውጭ ሀገራት የማስቀረት የፋይናንስ ወንጀል ድርጊት መፈፀም መሆኑን አስረድቷል።

ተቀማጭነታቸውን ከኢትዮጵያ ውጭ በማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሆኑ ግብረአበሮቻቸው ጋር በመመሳጠር በህጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ በውጭ ሀገራት በማስቀረት ክፍያውን በኢትዮጵያ ብር የሚፈፅሙ መሆናቸውም ተመላክቷል።

በተለይም ‘አዶሊስ’ ፣ ‘ሸጌ’፣ ሠላም ፣ ሬድ ሲ የተባሉና በውጭ ሀገር በገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር ላይ የተማሩት አካላት በህጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የነበረበትን የውጭ ምንዛሪ ለኢትዮጵያ ባንኮች የላኩ በማስመሰል ሀሰተኛ ደረሰኝ ጭምር በማዘጋጀትና በመጠቀም የውጭ ምንዛሪውን በውጭ ሀገራት በማስቀረት በኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ሀገራት ገንዘብ ምንዛሪና የኑሮ ውድነት እንዲባበስ በማድረግ ላይ ናቸው ብሏል አገልግሎቱ።

እነዚህ የገንዘብ አስተላላፊዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ግብረ አበሮቻቸው ከሆኑ ከ600 በላይ የሂሳብ ምንጮች በብር ክፍያ ሲፈፅሙ እንደነበርም መገለጹንም ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

እነዚህ አካላት ወደ ኢትዮጵያ በህጋዊ መንገድ መግባት የነበረበት ገንዘብ የኮንትሮባንድ ንግድን ጨምሮ ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች መፈፀሚያን እንዲውል በማድረግና በኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውም ተጠቁሟል።

የኢፌዲሪ ፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ፥ ህገወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባርን ጨምሮ መሰል የፋይናንስ ወንጀሎች የሚፈፅሙ አካላትንና በድርጊቱ የተሳተፉ ግብረ አበሮቻቸውን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከውጭ ሀገራት አጋር ተቋማት ጋር በማካሄድ ላይ ያለውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያሳወቀው፡፡

በዚህም አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የወንጀል ድርጊቱ ተዋናይና ተባባሪ የሆኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አገልግሎቱ አሳስቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.