Fana: At a Speed of Life!

ከጥላቻ ፍቅርን፣ ከመገፋፋት መቀራረብን ከራስ አልፎ ለሰዎች ማሰብን ከመስቀሉ ስራ መማር አለብን-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁላችንም ከጥላቻ ፍቅርን፣ ከመገፋፋት መቀራረብን ከራስ አልፎ ለሰዎች ማሰብን ከመስቀሉ ስራ መማር አለብን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡

የደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በደማቅ ሃይማኖታዊ ስነ- ስርዓት እየተከበረ ይገኛል፡፡

በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች ባስተላለፉት መልዕክት÷ የደመራ በዓል ከተማችንን የጎብኚዎች ተመራጭ ከተማ እንድትሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል ፤ ሃገራችንን ለዓለም ያስተዋወቀ አንዱ እና ትልቁ ባህላችንም ነው ብለዋል፡፡

እንዲሁም ፍቅር ፣ወዳጅነት፣አብሮነት የሚገለፅበት ህዝባችንንም ያስተሳሰረ ትልቅ በዓል ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ሰው ልጅ እውነተኛ ፍቅርን ከኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀሉ ፍቅር መማር ቢችል በዓለም ላይ ያሉ ፈታኝ ነገሮች ሁሉ መፍትሄ ያገኙ ነበር ያሉት ከንቲባዋ ዓለም በጥላቻ እና የመገፋፋት ሰለባ የሆነችው አንዱ ምክንያት ፍቅር ጎድሎ እራስ ወዳድነት በመብዛቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ሁላችንም ከጥላቻ ፍቅርን፣ ከመገፋፋት መቀራረብን ከራስ አልፎ ለሰዎች ማሰብን ከመስቀሉ ስራ በመማር መለወጥ አለብን ነው ያሉት፡፡

ይህንን በዓል ስናከብር በፍቅር በመተሳሰብ ለዘላቂ ሰላማችን መረጋገጥ እየሰራን፣ ጀግኖቻችንን እያከበርን፣ ደጀንነታችንን እያረጋገጥን፣ አንድነታችንን እያጸናን፤ እንደ ደመራው ደምቀን ጨለማ በሆነብን ነገር ሁሉ ላይ እያበራን በአሽናፊነት እንቀጥል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ሀገራችንም የሁሉንም ልጆቿን ፍቅር ትፈልጋለች ያሉት ከንቲባዋ በመሆኑም ለእውነቷና ለሉዓላዊነቷ እንዲሁም ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ህይወታችውን ሰጥተው ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ልጆች ያሏትና በኪዳን የፀናች ሀገር በመሆኗ ያጋጠማትን ፈተና ሁሉ እያሸነፈች በፅናት እንደምትቀጥል እናምናለን ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል እንደ መንግስት ከሁሉም ሃይማኖት ተቋማት ጋር እንደምናደርገው ሁሉ ከአንጋፋዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋርም በሰላም ፣በልማት ፣በብሄራዊ አገራዊ ጥቅሞችና በመከባበር አብረን መስራታችንን ከመቼውም በላይ አጠናክረን እንደምንቀጥል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ነው ያሉት ከንቲባዋ፡፡

ቤተክርስቲያኗ ለምታደርጋቸው ማንኛውም የበጎ ተግባር እንቅስቃሴዎችም ተገቢውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.