Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት የሰብአዊ ርዳታ ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት መጠቀሙን እንደቀጠለበት መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት የሰብአዊ ርዳታ ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት መጠቀሙን ቀጥሎበታል ሲል የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ የርዳታ ድርጅቶች ለርዳታ የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች በአሸባሪው ቡድን ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን እንዲያረጋግጡ መንግሥት በጥብቅ ያስገነዝባልብሏል ።

የሽብር ቡድኑ ቀደም ሲል ካገታቸው የሰብዓዊ ርዳታ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ በሥሩ የነበሩትንም የዓለም ምግብ ድርጅት እና የተመድ ዓርማ በመቀባት የጦር መሣሪያና ተዋጊዎችን በማመላለስ ለወታደራዊ ዓላማ እየተጠቀመ መሆኑን መግለጫው አስታውሷል።

መንግሥት የመከላከል ርምጃ ከሚወስድባቸው አካባቢዎች የርዳታ ድርጅቶች ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡም አስጠንቅቋል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

አሸባሪው ህወሓት የሰብአዊ ርዳታ ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት መጠቀሙን ቀጥሎበታል

መንግሥት ተገዶ የገባበትን የትግራይን ጦርነት በሰላም ለመቋጨትና ለክልሉ ዜጎችም ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ በርካታ ጥረቶችን ሲያደረግ ቆይቷል። ተግባራዊ ርምጃዎችንም ሲወስድ መቆየቱ ይታወቃል።

በአንፃሩ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ የተገኘ እርዳታን ለማድረስ ወደ ትግራይ ክልል የገቡ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት ዓላማ ሲጠቀምባቸው መቆየቱን መንግሥት በተደጋጋሚ ገልጿል። ርዳታውንም ለታጣቂዎቹ ግብዓት ሲያደርግ እንደነበር ተጋልጿል።

ዓለም አቀፍ ተቋማት በሽብር ቡድኑ የተፈጸሙና ዓለም አቀፍ ህጎችን የጣሱ ወንጀሎችን የማስቆም ኃላፊነት አለባቸው። እንዲሁም ወደ ክልሉ የሚገባ ድጋፍ ለተገቢው ዓላማ መዋሉን የማረጋገጥ ግዴታም ተጥሎባቸዋል። እነዚህ ዓለም አቀፍ የርዳታ ተቋማት የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ መንግስት ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡም ይታወሳል።

የህወሓት የሽብር ቡድን ሦስተኛ ዙር ወረራ መፈፀሙን ተከትሎ መንግሥት የሃገርን ህልውናና የዜጎችን ደህንነት ለማስከበር የመከላከል ርምጃ እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል። መንግሥት የመከላከል ርምጃ ከሚወስድባቸው አካባቢዎች የርዳታ ድርጅቶቹ ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ መንግሥት በድጋሚ ያስጠነቅቃል።

የሽብር ቡድኑ ቀደም ሲል ካገታቸው የሰብዓዊ ርዳታ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ በሥሩ የነበሩትንም የዓለም ምግብ ድርጅት እና የተመድ ዓርማ በመቀባት የጦር መሣሪያና ተዋጊዎችን በማመላለስ ለወታደራዊ ዓላማ እየተጠቀመ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም የርዳታ ድርጅቶች ለርዳታ የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች በአሸባሪው ቡድን ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን እንዲያረጋግጡ መንግሥት በጥብቅ ያስገነዝባል ።

መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.