በመዲናዋ የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም መጠናቀቁን ፖሊስ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይና በተለያዩ ቦታዎች የተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ/ም የኃይማኖት አባቶች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይና በተለያዩ ቦታዎች የተከበረው የደመራ በዓል በሰላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የፀጥታ አካሉ ዕቅድ በማውጣት በርካታ የሰው ኃይሉን በመከላከል ስራ ላይ ማሰማራቱን፤ ከበዓሉ አስተባባሪዎች ጋር በቅርበት በጋራ በመሰራቱ በአዲስ አበባ የተካሄደው የደመራ በዓል ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ መከበሩን ፖሊስ ገልጿል፡፡
በመስቀል አደባባይ የተካሄደውን የደመራ በዓል ተከትሎ በከተማችን በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እና በአንዳንድ ስፍራዎች የተከበረው የደመራ የማብራት ስነ-ስርዓት ካለ አንዳች የፀጥታ ችግር በሰላም መካሄዱን ነው የተገለጸው፡፡
ህብረተሰቡ የፀጥታው ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል አመለካከት በመያዝ ለፀጥታው ስራ ስኬታማነት ላሳየው ቀና ተባባሪነትና ጨዋነት እንዲሁም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለተወጡ በየደረጃው ለሚገኙ ለመላው የፀጥታ አካላት ለአመራርና አባላቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምስጋና አቅርቧል፡፡
ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስራ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪ አቅረቧል፡፡
የመስቀል በዓልም በሰላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ራሱንና አካባቢውን ከወንጀልና ከትራፊክ አደጋ እንዲጠብቅም ጥሪ ማስተላለፉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡