በአማራ ክልል የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 925 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 925 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የአማራ ክልል ንግድና ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ የከኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገሪቱ መግባቱን ተከትሎ አንዳንድ የንግድ ተቋማት አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
መሰል ሁነቶችን በመጠበቅ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ የንግድ ተቋማትን ለመቆጣጠርም ከዞን እስከ ወረዳ ድረስ ግብረ ሃይል መቋቋሙን ነው የገለጹት።
እስካሁን በክልሉ በተደረገ የቁጥጥር ስራም በተለያዩ ሸቀጦች ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 925 የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን ተናግረዋል።
ከድርጊቱ ጋር በተያያዘም 16 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፥ ይሁን እንጅ የአልኮል እና የፊት መሸፈኛ ጭምብል አቅርቦት ችግር መኖሩን አንስተዋል።
በናትናኤል ጥጋቡ