Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ ደኅንነት ቁጥጥር ኦዲት ፕሮግራም ዓለም አቀፍ ሽልማትና እውቅና ተሰጣት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ ደኅንነት ቁጥጥር ኦዲት ፕሮግራም ከዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት እውቅና ተሰጣት፡፡

በካናዳ ሞንትሪያል እየተካሄደ ባለው 41ኛው የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ጉባዔ÷ ኢትዮጵያ በሲቪል አቪዬሽን ሁለንተናዊ ደኅንነት ቁጥጥር ኦዲት ፕሮግራም የምክር ቤት ፕሬዚዳንት የምስክር ወረቀት ሽልማትና እውቅና ተበርክቶላታል፡፡

ሽልማቱን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ከዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ካውንስል ፕሬዚዳንት ሳልቫቶሬ ስኪያቺታኖ ተረክበዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የምስክር ወረቀት የተበረከተላት ከአባል ሀገራቱ መካከል በዓለም ዓቀፍ የደኅንነት ክትትል ኦዲት ፕሮግራም ላስመዘገበችው ውጤት መሆኑ ተገልጿል፡፡

እውቅናና ሽልማቱ በሲቪል አቬዬሽን መስክ ደኅንነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ስኬት ላስመዘገቡ አባል ሀገራት የሚበረከት መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በተደረገው የደኅንነት ማረጋገጥ ሂደትም ከእያንዳንዱ የዓለም ዓቀፉ ሲቪል አቪዬሽን አባል ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት የቁጥጥር ጉድለቶች ነፃ መሆኗ ተገልጿል፡፡

የደኅንነት ቁጥጥር ስርዓቶችን በውጤታማነት በመተግበሯ ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ያስቀመጣቸውን ደረጃዎች እና የሚመከሩ ልማዶችን መተግበር በመቻሏ እውቅናው ተሰጥቷታል፡፡

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት እውቅናው ሳይሰጥ በመቆየቱ ዘንድሮ እየተካሄደ ባለው ጉባዔ ላይ÷ ከፈረንጆቹ 2019 እስከ 2022 በአቪዬሽን ደኅንንነት ዙሪያ ኢትዮጵያ ከአባል ሀገራቱ መካከል ላስመዘገበችው ስኬት እውቅና እንዲሰጣት ተወስኗል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.