Fana: At a Speed of Life!

የግሸን ደብረ ከርቤ የንግሥ በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መስከረም 21 ቀን 2015 ዓ.ም የሚከበረው የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግሥ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር እርገጤ ጌታሁን ባለፉት ዓመታት በኮሮና ወረርሽኝ እና የሽብር ቡድኑ ህወሓት በከፈተው ጦርነቱ ምክንያት ብዙ ምዕመናን መምጣት አለመቻላቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ዓመት ግን አካባቢው ሰላማዊ በመሆኑ በርካታ ምዕመናን ወደ አካባቢው ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲከበር በቂ ሥምሪትና ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡

ከደሴና ኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ፣ አድማ ብተና እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የጋራ ዕቅድ አውጥተው እየሠሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ከምዕመናን ጋር ሰርጎ ገቦች ተቀላቅለው ሊመጡ ስለሚችሉ የጸጥታ ኃይሉ ከወትሮው በተለየ ዝግጅትና ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስችል የኃይል ሥምሪት መደረጉን ተናግረዋል።

በዋነኝነት ትልቅ አቅም የሚሆነው ምዕመናንና ማህበረሰቡ ነው ያሉት ረዳት ኮሚሽነሩ÷ የተለየ እንቅስቃሴና ጥርጣሬ ሲያጋጥመው ለፖሊስ ጥቆማ እዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ምዕመኑ ለስርቆትና ለመሰል መጭበርበሮች ተጋላጭ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።

በበዓሉ ዕለት በአካባቢው የተሽከርካሪ መጨናነቅ እንዳይፈጠርና ለጸጥታ ሥራው ምቹ እንዲሆን የትራፊክ ፖሊስ መሰማራቱንም ገልጸዋ፡፡

እንግዶች ወደየአካባቢያቸው እስከሚመለሱ ድረስ እንደወትሮው ሁሉ ተንከባክበን እንግዶችን በማስደሰት መሸኘት ይኖርብናል ሲሉ ለአካባቢው ማህበረሰብ ጥሪ አቀርበዋል፡፡

እንግዶች የጸጥታ አካላትን እገዛ ለማግኘትና ጥቆማ ለመስጠት +251-985-14-84-11/+251_331-11-55-76/+251-922-89-98-46 በመደወል ማሳወቅ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.