Fana: At a Speed of Life!

ወርቃማው ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ሲታወስ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ አዘዞ ተወልዶ በሦስት ወሩ  ወደ  ደቡብ ጎንደር  ዞን ደብረታቦር ከተማ ሄዶ እዚያው አደገ፡፡

 

አብሮት የኖረው ስሙ ማዲንጎ ይሁን እንጂ ፥ እናትና አባቱ ያወጡለት መጠሪያ ስም “ተገኔ” ነበር፤ “ጠበቃዬ ፥ ጋሻ መከታዬ ማለት ነው” ብሎ ነበር ራሱ ማዲንጎ።

 

ማዲንጎ በተለያዩ ጊዜያት ባደረጋቸው ቃለ ምልልሶች አባቱን ጨምሮ  አብዛኛው ቤተሰቡ የቤተ ክህነት አገልጋይ የነበሩ መሆናቸውን ተናግሯል።

 

በልጅነቱ የሙዚቃ ፍቅር እንዳደረበት ይናገር የነበረው ማዲንጎ፥ የሰባተኛ ክፍለ ጦር ካምፕ የ603 ኮር  የሙዚቃ ቡድን ልምምድ ሲያደርግ ከተመለከተ በኋላ ድምጻዊ መሆን እችላለሁ በማለት እድል እንዲሰጡት ጠይቆ እንደነበርም ነው በቃለ ምልልሶቹ የተናገረው።

 

እናም በወቅቱ እድሉን አግኝቶ የድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩን ” ና ተላክ ልቤ ፥ ልላክህ ልስደድህ ልቤ” የተሰኘውን  ሙዚቃ  ተጫውቶ  አድናቆት ተችሮታል፡፡

 

ተቀባይነትን አግኝቶም በዛው በወታደር ቤት ሙዚቃውን የቀጠለ ሲሆን፥ “ማዲንጎ” የሚለው ስሙም እዛው  እንደወጣለት ነው የገለጸው።

 

ማዲንጎ በአንድ ወቅት ኤፍሬም ታምሩ እንደ ዓርአያ (ሞዴል) የሚመለከተው እና  በዋናነትም የኤፍሬም ስራዎች ወደ ሙዚቃው ዓለም ለመግባት ምክንያት እንደሆኑት እና በብዛት የእርሱን ስራዎች እንደሚጫወትም ነው ይናገር የነበረው።

 

በተጨማሪም ሙሉቀን መለሰን፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣  ፀጋዬ  እሸቱ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ይሁኔ በላይ፣ ኤልያስ ተባባልን እንደሚያደንቅ እና የእነሱን ሙዚቃዎች እንደሚጫወት አውርቷል።

 

 

ማዲንጎ በታዳጊ የኪነት ቡድን ከዚያም በወታደር ቤት ብዙ ጊዜን ካሳለፈ በኋላ ኑሮውን ባህርዳር ከተማ በማድረግ ድምፃዊ የመሆን ህልሙን መስመር  አስያዘ፡፡

 

በይፋ ወደ ሙዚቃው ዓለም በተቀላቀለባት ባህር ዳር ከተማም በ120 ብር ወርሃዊ ደመወዝ ተቀጥሮ ቤተሰቡን እያገዘ ይኖር ነበር።

 

በመቀጠልም ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት የተለያዩ  የሙዚቃ ባንዶችን በመቀላቀል የታዋቂ ሙዚቀኞች ስራዎችን በማቀንቀን ተወዳጅነትን አገኘ፡፡

 

በሂደትም በ1987 ዓ.ም “ስያሜ አጣሁላት” የተሰኘውን እና እሱ የልጅነቴና ከሰው ጋር አስተዋወቀኝ የሚለውን አልበሙን ለህዝብ ጆሮ አደረሰ፡፡

 

በዚህም አድናቆትን እና የህዝብ ፍቅርን ሲያገኝ ከዓመታት በኋላ “አይደረግም” የተሰኘውን ሁለተኛ  አልበሙን ለህዝብ በማድረስ ተወዳጅነቱን ከፍ አደረገ።

 

ይህ አልበሙም አይደረግም፣ የአፋሯ ቆንጆ፣  ሰው የለኝም ፣ ማህሌት፣ ሞኙ ልቤ  እና ሌሎች ተወዳጅ ዜማዎችን ያካተተ ነው።

 

ድምፀ መረዋው አርቲስት ማዲንጎ፥  በመልዕክትም ሆነ በይዘት ጠንካራ መልዕክት ያላቸውን በሀገር፣ በፍቅር፣ በትዝታ እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተለያዩ  ቅኝቶች አቀንቅኗል፡፡

 

በተለያዩ የዓለም ሀገራት በመዘዋወርም ለአድናቂዎቹ ስራዎቹን በማቅረብ በውጭ የሚኖሩ በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵታውያን ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡

 

በሂደትም  “አይደረግም” የተሰኘውን ሁለተኛውን አልበሙን ካወጣ ከስምንት ዓመት በኋላ “ስወድላት” የተሰኘውን ሦስተኛ  አልበሙን ለአድማጭ እንካችሁ አለ።

 

በዚህ የሙዚቃ አልበሙ ውስጥ ላላተርፍ፣ ስወድላት፣ አቅሜን፣ አይሆንልኝም፣ እባክሽ ታረቂኝ፣ ከተለያየን ፣ ውሰጃት፣ ዳኛ፣ ጎዳናው፣ ማተቧ፣ ማርማር የተሰኙና ሌሎች  ሙዚቃዎች ተካተዋል፡፡

 

በስወድላት አልበምም  በተለያዩ  የሙዚቃ ውድድሮች እጩ እንዲሁም  “ምርጥ የፍቅር አልበም“ ተብሎ  መሸለም ችሏል፡፡

 

“ ተንገበገበልሽ አረረልሽ ሆዴ፣

 

አትራቂኝ በእኔ ሞት አይብዛ መንደዴ፣

 

ያስታርቀን መውደዴ ፣

 

ልመናዬን ስሚኝ ይቅርታሽ  ይድረሰኝ፣

 

ጥፋቴን ለመርሳት እኔ አቅም አነሰኝ፤…. “

 

የሚለውና በሦስተኛው አልበሙ ውስጥ የተካተተው የፍቅር ሙዚቃው ህዝብ ልብ ውስጥ ከቀሩ ተወዳጅ ስራዎቹ ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡

 

“መቼም ከሀገሩ ከቀዬው ርቆ

ሰው ከሀገሩ ቢሄድ ርቆ ቢሄድ ርቆ

 

ልቡ ቀልብ ሃሳቡ መች ይረጋል (2x)

 

ልቡ ከሱ መች ሊረጋ መች ሊረጋ ፣

 

የሰው ሀገር የሰው ነው እንደራስ አይሆንም ፣

 

ቢከፋውም ቢቸገርም ቢያዝንም ብቻውን ነው ፤”

 

የተሰኘው ስለሚወዳት ሀገሩ ያዜመው ዜማ ደግሞ  በተለይም ከሀገር ርቀው በሚኖሩ የሀገሩ ልጆች  ዘንድ በእጅጉ ተወዳጅ ነው፡፡

 

እንዲሁም  ከአልበሞቹ በተጨማሪ “በላይ”፣ ከብርሃኑ ተዘራ ጋር የተጫወተው “ሰላም ያገር ሰው”፣ ለ“ዓባይ ወይስ ቬጋስ” ፊልም  የሰራው ማጀቢያ ሙዚቃ ከሰራቸው ስራዎቹ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው ይጠቀሳሉ።

 

“በማንኛውም ሙያ ውስጥ ያላችሁ  ወጣቶች፥  በጥረት እንጂ  ከመሬት ተነስቶ የሚመጣ ነገር የለም፤ በድንገት የሚመጣ  ነገርም ጠቃሚ አይደለም” በማለት ያስተላለፈው መልዕክትም የሚታወስ ነው።

 

አርቲስት ማዲንጎ አራተኛ አልበሙን ለአድማጮች ለማድረስ በመስራት ላይ እንደነበርም ነው የተሰማው። አይቀሬው ሞት ድንገት ፈጥኖ ቀደመው እንጂ።

 

በተለይም ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ወቅት እያመመው ግንባር ድረስ በመሔድና በማሰልጠኛ የሚገኙ ምልምሎችን በማነቃቃት የራሱን ታሪክ የሰራ ብርቅዬ አርቲስት ነበር።

 

ግንባር ድረስ በመዝመትም ማዲንጎ አፈወርቅ በወርቃማ ድምጹ አገር ወዳድ ወጣቶችን ሳይሰስት አዝናንቷል።

 

ለዚህም በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  እጅ እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡

 

አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ በወጣትነቱ እና ብዙ መስራት በሚችልበት ዕድሜው ባደረበት ህመም  ምክንያት በትናንትናው ዕለት በስጋ ተለይቶናል።

 

ሆኖም በምርጥ አይረሴ  የጥበብ ሥራዎቹና በፍሬ ልጁ ዘወትር ስናስታውሰው እንኖራለን፥፡፡

 

አርቲስቱ የአንድ ሴት ልጅ አባትም ነበር፡፡

 

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም በድምፃዊው ሕልፈተ ሕይወት የተሰማውን ሐዘን በድጋሚ እየገለፀ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ለአድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል፡፡

 

በፌቨን ቢሻው

 

 

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.