Fana: At a Speed of Life!

አገራዊ የምክክር ሂደቱን በገንዘብ ለመደገፍ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አገራዊ የምክክር ሂደቱን በገንዘብ ለመደገፍ የሚያስችል የፕሮግራም ሰነድ ስምምነት በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽንና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም መካከል ተፈረመ፡፡

ለሦስት ዓመታት ተግባራዊ በሚደረገው በዚህ የፕሮግራም ሰነድ፥ የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ከልማት አጋሮች ፈንድ ለማሰባሰብ የፋይናንስ ቋት በመክፈት የሚያስተዳድር መሆኑ ተገልጿል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በበኩሉ እንደ አንድ የልማት አጋር አገራዊ የምክክር ሂደቱን በገንዘብ ለመደገፍ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር መመደቡ ታውቋል፡፡

የልማት ፕሮግራሙ በሚከፍተው የፋይናንስ ቋት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ከልማት አጋሮች 32 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ገንዘብ ለማሰባሰብ ታቅዷል፡፡

መንግስት ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከሚመድበው ዓመታዊ በጀት በተጨማሪ፥ ይህ በተባባሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በሚከፈተው የፋይናንስ ቋት ከልማት አጋሮች የሚሰበሰበው ፋይናንስ ነጻ በሆነ የባለአደራ ፈንድ (ትረስት ፈንድ) እንደሚተዳዳርም ተገልጿል፡፡

የትረስት ፈንዱ መቋቋም አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተልእኮውን እንዲወጣ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ አንደታመነበት ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.