Fana: At a Speed of Life!

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሽብርተኝነትን በመዋጋት ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በትብብር የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሃሙድ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ዛሬ በጎበኙበት ወቅት ከዚህ ቀደም ሽብርተኝነትን በመዋጋት እና በመረጃ ልውውጥ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በትብብር ይከናወኑ የነበሩ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ሽብርተኝነትን ለመመከት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተች የምትገኝ ሀገር መሆኗን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ ÷ቀጣናው የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን የትብብርና የአጋርነት አድማሶችን በማስፋት የተለያዩ ተግባራት በጋራ እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሃሙድ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ለሶማሊያ ሰላም ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡

የሶማሊያም መረጋጋት በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን የጎላ ሚና ያበረክታል፤ ሁለቱ ሀገራት በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የሚያከናውኗቸው ተግባራት ከአካባቢው አልፎ ለአፍሪካም ጠቃሚ በመሆኑ ሽብርተኝነትን፤ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችም፤ ሕገወጥ የጦር መሣሪያና የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል የሚረዱ የመረጃ ልውውጦች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባደረጉት ጉብኝት በተቋማዊ ሪፎርሙ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ፣ዘመናዊ አሠራር በመዘርጋት፣ በአጋርነትና በትብብር መስኮች አስደናቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን እንደተመለከቱ የገለጹት ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሃሙድ ትልቅ ልምድ ማግኘታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ሶማሊያም በአቅም ግንባታና በሌሎችም መስኮች ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በትብብር እንደምትሠራ ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ውጤታማ የደኅንነት ዘርፍ ሪፎርም እንዲካሄድ ላበረከቱት አስተዋጽዖም ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ በጉብኝቱ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት÷በኢትዮጵያና በሶማሊያ መንግሥታት መካከል ካለው ጠንካራ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት ባሻገር ሁለቱ ሀገራት ተመሳሳይ ባሕል፣ ቋንቋና ሃይማኖት የሚጋሩ በመሆናቸው የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩም ጠንካራ ነው፡፡

ሶማሊያ የኢትዮጵያ ቁልፍ ስትራቴጂክ አጋር የሆነች ሀገር መሆኗን ያመለከቱት አቶ ሲሳይ፤ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሰላም አስከባሪ በመላክ ቀጣናው የተረጋጋ እንዲሆን ያበረከተችውን ሚና እንደ መገለጫ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጣይም በወታደራዊና በደኅንነት መስኮች ትብብሩን በማጠናከር ቀጣናው የተረጋጋ እንዲሆን ቁርጠኛ አቋም ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሲሳይ ማብራሪያ፤ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከሶማሊያ አቻ ተቋም ጋር በአቅም ግንባታና በመረጃ ልውውጥ መስኮች የሚደረጉ ትብብሮችን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

በዚህም በቀጣናው የሚታዩ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፤ ሕገወጥ የገንዘብ፣ የጦር መሣሪያና የሰዎችን ዝውወር ተጽዕኖ መቀነስ ይቻላል፡፡

እንደ አልሸባብ ያሉ የሽብር ቡድኖችን ለመከላከል ከውስጥ ባለድርሻ አካላትና ከውጭ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር በመተባበር ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን÷ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ኢትዮጵያ በውጫዊና ውስጣዊ ተግዳሮቶች ብትፈተንም ውጤታማ የደኅንነት ዘርፍ ሪፎርም ማካሄዷን የገለጹት አቶ ሲሳይ፤ በዚህም ፕሮፌሽናል ተቋም መገንባት፤ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት፤ የዘመኑን የደኅንነት ስጋት የሚመክቱ የቴክኖሎጂ አቅሞች ማልማትና መጠቀም፤ አጋርነትና ትብብርን ማጠናከር እንዲሁም የሥነ ልቦና ጦርነትን በብቃት መመከት መቻሉን አመልክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.