የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲስ አበባ የኢሬቻ በዓል የሚከበርበትን ቦታ የማጽዳት ስራ ተከናወነ

By Melaku Gedif

September 29, 2022

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የኢሬቻ በዓል የሚከበርበትን ቦታ  የማጽዳት ስራ በዛሬው ዕለት ተከናውኗል፡፡

የጽዳት መርሐ ግብሩ የአዲስ አበባ  ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣  የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት ነው የተከናወነው፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ÷ የኢሬቻ በዓል የሰላም፣ የአብሮነት፣ የተለያየ የሚገናኝበት፣ ከሁሉ በላይ ፈጣሪ የሚመሰገንበት በመሆኑ ሁላችንም ተቀራርበን አብሮነታችንን ከፍ እያደረግን አንድነታችንን እያፀናን ልናከብር ይገባል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ በዘመን መለወጫ ፣ በመስቀል በዓል  እና በመሳሰሉት በከፍተኛ ርብርብ የጋራ በዓላችን ነው በማለት በመቀራረብ፣ በአብሮነት በጎ እሳቤ እንድናከብረው አድርጓልም  ነው ያሉት ከንቲባዋ፡፡

የኢሬቻን በዓልም ህብረተሰቡ  በተመሳሳይ ስሜት በመተሳሰብና በመከባበር እንዲያከብረው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዓልን እየጠበቁ  ከተማዋን  የሁከት ማዕከል ለማድረግ የሚጥሩ የሁከት ነጋዴዎች ለአፍታም ቢሆን ሳንታገስ ማጋለጥ አለብን ማለታቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡