Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት 77ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ወሳኝ አቋሞቿን አስረድታለች -የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስታቱ ድርጅት 77ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና በሰሜኑ ጦርነት ጉዳይ አቋሟን ያስረዳችበት እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በጉባኤው ኢትዮጵያ ወሳኝ ያለቻቸውን አቋሞች ማስረዳቷን አንስተዋል።

በተለይም ከህዳሴ ግድብ እና ሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ አቋሟን አስረድታለች ነው ያሉት።

በዚህም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኩል የሰሜኑ ጦርነት በሰላም ለመፍታት እንዲሁም የህዳሴ ግድብን በተመለተ የጋራ ተጠቃሚነት ጋር በተገናኘ ተጠቃሚነቱም መፍትሄውም አፍሪካዊ ስለመሆኑ ያስረዳችበት መሆኑን ገልፀዋል።

ዓለም ላይ ያለን ችግር ለመፍታት ከተናጠል አካሄድ ይልቅ የጋራ ጉዞ እንደሚያስፈልግ ያስገነዘበችበት ነው ብለዋል።

ከጉባኤው ጎን ለጎንም የሀገራት መሪዎች ጋር ግንኙነት በማድረግ የሁለትዮሽ ውይይቶች እንደነበሩ ጠቅሰው፥ 20 የሚሆኑ ውይይቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የሆነችባቸው በአረንጓፌ አሻራ እና በሰቆጣ ቃል ኪዳን ውስጥ የተካተቱ ስራዎችን አጀንዳ ማድረግ ያስቻሉ መድረኮች እንደነበሩ በተለይም ኢትዮጵያ ልምዷን ያካፈለችበት ስለመሆኑም አመላክተዋል።

ከዚህ ባለፈም ቻይና፣ ህንድ፣ ሩሲያ፣ ኤርትራ እና ማሊን ጨምሮ ከበርካታ ሀገራት መሪዎች ጋር በመገናኘት የሀገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ጠቁመዋል።

የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋርም በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ መሆኑን ያነሱት ቃል አቀባዩ፥ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መወያየታቸውን ጠቁመዋል።

በውይይታቸውም አሸባሪነትን በመዋጋት እና በንግድ ትስስር ዙሪያ አብረው ለመስራት መስማማታቸውን ነው የገለጹት።

በሃብታሙ ተክለስላሴ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.