Fana: At a Speed of Life!

የአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ የሕይወት ታሪክ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ከእናቱ ከወይዘሮ ሀገርነሽ ዋሴ እና ከአባቱ አቶ አፈወርቅ መንግሥቱ በ1970 ዓ.ም በጎንደር አዘዞ ተወለደ፡፡

በተወለደ በሶስት ወሩም ወላጆቹ ኑሯቸውን በደብረታቦር ከተማ አድርገው በዚያም እድሜው ሲደርስ በደብረታቦር ከተማ ከዘመናዊ ትምህርት ጋር ተዋውቋል፡፡

በዘጠኝ አመቱ ማይክ የጨበጠው ማዲንጎ ከ603ኛ ክፍለ ጦር አባላት ጋር ወደ ባሕርዳር በማቅናት ዛሬ የደረሰበትን የሙዚቃ ህይወት አንድ ብሎ ጀምሯል።

ከባሕር ዳር ቆይታው በኋላም ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ከአምስቱ እርጎየዎች እና ከላፎንቴኖች ጋር ሲሰራ ቆይቷል።

ማዲንጎ በ1989 ዓ.ም ከሁለት ጓደኞቹ ጋር የቲሸር ባንድ አልበሙን በማሳተም ለህዝብ ጆሮ ያደረሰ ሲሆን፥ በ1991 ዓ.ም በ“ስያሜ አጣሁላት” አልበሙ አማን ነወይ ጎራው የሚለው የሙዚቃ ስራው ይበልጥ ተወዳጅነትን አትርፏል።

በ1997 ዓ.ም በኤልያስ መልካ ተቀናብሮ ለሕዝብ ጀሮ የደረሰው “አይደረግም” አልበም እንዲሁም በ2007 ዓ.ም ስወድላት የሚለውን አልበም በተስረቅራቂ ድምጹ ሥራውን በማቅረብ አድናቆትን አትርፏል፡፡

ከአልበሞቹ በተጨማሪም በላይ፣ ከብርሃኑ ተዘራ ጋር የሰራው “ሰላም ያገር ሰው” እና “አባይ ወይስ ቬጋስ” በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ ስራዎቹ ናቸው።

ሀገር አጣብቂኝ ውስጥ በገባችበት ወቅት ግንባር ድረስ ወርዶ ጀግኖችን በማበረታቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡

ማዲንጎ አፈወርቅ ባለትዳር እና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ሲሆን በማኅበራዊ ሕይወቱም ለበርካቶች መጠጊያ፣ ደግ፣ ሩህሩህ እና አዛኝ እንደነበር የቅርብ ወዳጆቹ እና የሙያ ባልደረቦቹ ይናገራሉ።

በጡረታ የተገለሉ የሙያ አባቶች እና እናቶችን በመጠየቅ ቀዳሚው እንደነበር የሚነገርለት አርቲስት ማዲንጎ፥ አራራይ የሙዚቃ የመረዳጃ ማኅበር መስራች እና አባልም ነበር፡፡

ማዲንጎ አዲስ አልበም ለማሳተም ዜማ እና ግጥም አጠናቆ እንደነበርም ለማወቅ ችለናል፡፡

ተወዳጁ አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ በተወለደ በ44 ዓመቱ መስከረም 17 ቀን 2015 ዓ.ም በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.