የሶማሊያው ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን ጎበኙ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሃሙድ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋናው መስሪያ ቤት ተገኝተው የስራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በመሆን በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ሲደርሱ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ማኔጅመንት አባላት በፖሊሳዊ ሥነ-ሥርዓት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የታጠቃቸውን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅሞችን እና ተቋሙ አሁን የደረሰበትን የለውጥ ደረጃ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ከጉብኝቱ በኋላም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ጋር የሁለቱን ሀገራት የፖሊስ ኃይል ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሶማሊያ ፖሊስ ወጣት መኮንኖች ገብተው እንዲማሩና እንዲሰለጥኑ ፕሬዚዳንቱ ያቀረቡትን ጥያቄ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ተቀብለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ጠንካራ የጋራ የፀጥታ ግብረ ኃይል አቋቁመው በድንበር አካባቢ የጋራ ጥበቃ ለማድረግ እና በሽብርተኝነት ላይ የተጀመረውን ዘመቻ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሃሙድ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እየተከናወነ ባለው ሪፎርም መደሰታቸውንና ስለተመለከቱት የለውጥ ሥራም አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ፖሊስ ልምዱን በማካፈል እገዛ እንዲያደርግ መጠየቃቸውንም ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡