Fana: At a Speed of Life!

በአዳማ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ 82 የአሸባሪ ቡድኖቹ ተላላኪዎች በቁጥጥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዳማ ከተማ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ 82 የአሸባሪዎቹ ሸኔና ህወሓት ተላላኪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የከተማዋ ፀጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ገለፀ።

የአዳማ ከተማ ፀጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሀላፊ መኩሪያ ድንቁ እንደገለጹት÷ የአሸባሪው ሸኔና የህወሓት ተላላኪዎች በከተማዋ መስቀልና ኢሬቻን ጨምሮ ህዝባዊ በዓላትን ለማወክ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር።

33 የአሸባሪው ሸኔና አባ ቶርቤ አባላት እና 49 የአሸባሪው ህወሓት ሴሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

በመጪው ቅዳሜና እሁድ በሆራ ፊንፊኔና ቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ መስተዳደሩ ከምሥራቅ ሸዋ ዞንና አጎራባች ከተሞች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይ የተቀናጀ የፀጥታ አካላት ስምሪት በመስጠት የፀጥታ ሃይላትን በአንድ ላይ በከተማዋ በአራቱም መግቢያና መውጫ ቦታዎች ላይ በቅንጅት የፍተሻ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም 19 ሽጉጦች፣ 6 ክላሽና ከ3ሺህ በላይ የተለያዩ ተተኳሽ ጥይቶች መያዛቸውን አመልክተዋል።

በከተማ ደረጃ ያለውን የፀጥታ ምክር ቤት እስከ ቀበሌ ድረስ በማጠናከር በየሳምንቱ ግምገማ እያከናወኑ መሆኑም ጠቅሰዋል።

“አባ ቶርቤ” ተብሎ ወደ ከተማዋ የገባውና በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ ኬንያ ላይ በአሸባሪው ሸኔ ወታደራዊ ስልጠና ወስዶ ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር የመጣ መሆኑን ሀላፊው ምግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአዳማም ሆነ በዙሪያዋ የሰርጎ ገቦችን እንቅስቃሴ ለማምከን ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል።

 

 

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.