Fana: At a Speed of Life!

10ኛው የጣና ፎረም ጉባዔ ለባሕርዳር ከተማ ገፅታ ግንባታ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል- አቶ ጣሂር ሙሃመድ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በባሕርዳር ከተማ የሚካሄደው 10ኛው የጣና ፎረም ጉባዔ ለከተማዋ ቱሪዝም ዕድገትና ገፅታ ግንባታ ልዩ ቦታ እንደሚሰጠው የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጣሂር ሙሃመድ ተናገሩ፡፡

አቶ ጣሂር ከጣና ፎረሙ ጉባዔ መካሄድ ጋር በተያያዘ በሰጡት መግለጫ÷ ጉባዔው ከጥቅምት 4 እስከ 6 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

በጉባዔው ላይም÷ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ የቀድሞ መሪዎች፣ ተፅእኖ ፈጣሪዎች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችን ጨምሮ በአጠቃላይ 280 የሚሆኑ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የጉባዔው በባሕርዳር ከተማ መካሄድም÷ ለከተማችን ቱሪዝም ዕድገትና ገፅታ ግንባታ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ነው ብለዋል፡፡

ጉባዔውን በብቃት በማስተናገድ ከተማችን በቱሪዝም ኮንፈረንስ የበለጠ እንድትታወቅ ማድረግ ይጠበቅብናልም ነው ያሉት፡፡

ለዚህም የክልሉ መንግሥት እና የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለፎረሙ መሳካት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አቶ ጣሂር አረጋግጠዋል፡፡

የዘንድሮው የጣና ፎረም ጉባዔ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አስመልክቶ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ከጣና ፎረም አዘጋጅ ኮሚቴ ጋር መስከረም 6 ቀን 2015 ዓ.ም መወያየታቸው ይታወሳል፡፡

ጣና ፎረም ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪካ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለማፈላለግ የተቋቋመ እና በአፍሪካ ኢኮኖሚ፣ ሰላም፣ ንግድ ትስስር እና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ዙሪያ የሚመክር አፍሪካዊ ነጻ ተቋም ነው፡፡

የአፍሪካ መሪዎች በአፍሪካ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረው አቅጣጫ የሚያስቀምጡበት ጣና ፎረም በየዓመቱ በባሕርዳር ከተማ እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.