Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የኢሬቻ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የኢሬቻ በዓል አከባበር በተለያዩ ዝግጅቶች በሁሉም ክፍለከተሞች መከበሩን ቀጥሏል፡፡
በዓሉን በማስመልከትም በዛሬው ዕለት በሁሉም ክፍለ ከተሞች የፓናል ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማና በአጎራባቹ የለገጣፎ ከተማ በጋራ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በጋራ የሚያከብረው የምስጋናና የፍቅር የአንድነትና ህብረት በዓል መሆኑ ነው የገለጹት፡፡
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ÷የምስጋና፣ የሰላምና የይቅርታ መገለጫ የሆነውን የእሬቻ በዓል ስናከብር ለሀገር ሰላምና ልዕልና አካልና ህይወቱን ያለስስት እየሰጠ ለሚገኘው ጀግናው መከላከያ ሰራዊት ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
የገዳ ስርዓት የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ባህል መገለጫ ነው ያሉት ከንቲባዋ÷ የስርዓቱ አካል የሆነው ኢሬቻ የተለያየ የሚገናኝበት ፤ ጨለማው አልፎ ብራ የሚሆንበት ፤ ወደ አዲስ ተስፋ የሚሸጋገርበት ትልቅ በዓል መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የለገጣፎ ከተማ ም/ከንቲባ ክፍሌ ጨልቀባ በበኩላቸው ይህ በዓል ኦሮሞ ብቻውን ተነጥሎ የሚያከብረው በዓል አይደለም ያሉ ሲሆን ፥ በጋራ የምናከብረውና አብሮነታችንን እንዲሁም አንድነታችንን የምናሳይበት ነው ብለዋል፡፡
በዓሉ የህዝብ በመሆኑ እንግዶችን በመቀበል በዓሉን በሰላም እንዲያከበሩ እንደሚያደርጉ የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡
የኢሬቻ በዓል የፖለቲካ መልዕክት የሚተላልፍበት ሳይሆን ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በመሆኑ ወጣቶች ባህላዊና ትውፊታዊ ስርዓቱን ጠብቀው ማክበር እንዳለባቸው የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.