Fana: At a Speed of Life!

ቆሼ አካባቢ በደረሰ የእሳት አደጋ 60 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬዉ ዕለት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 በተለምዶ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው ቦታ ከቀኑ 10:34 አካባቢ በደረሰ የእሳት አደጋ 60 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት አደጋው የደረሰው የተቃጠለ ዘይትን መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውል ፋብሪካ ላይ ነው ብለዋል ።

በዚህም 60 ሚሊየን ብር የተገመተ ንብረት ሲወድም አንድ የእሳት አደጋ ሰራተኛን ጨምሮ አምስት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል ነው ያሉት ።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የአካባቢዉ ህብረተሰብና የጸጥታ ሀይሎች በጋራ ባደረጉት ርብርብ እሳቱ በአቅራቢያው ወደሚገኙ መነኮሳት መኖሪያ ቤቶች ተዛምቶ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ እንደተቻለ ነው አቶ ንጋቱ ያስረዱት ።

በዚህ ሂደትም 350 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን ተችሏል ብለዋል ።

አደጋዉን ለመቆጣጠር 10 የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪና 2 አምቡላንስ እንዲሁም 80 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሰማርተው እንደነበር ያነሱት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው፥ የእሳት አደጋውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠርም 2 ሰዓት ፈጅቷል ነው ያሉት ።

ፋብሪካዉ የተገነባበት ስፍራና በውስጡ የያዛቸዉ ተቀጣጣይ ዘይቶችና ከፍተኛ የሆነ የተቃጠለ
ዘይት ክምችት ለእሳቱ መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደነበረውም አቶ ንጋቱ ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካዉ ከአደጋ ደህንነት አንጻር አሁንም ስጋት ውስጥ ይገኛል ነው የተባለው ።

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.