Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል ተከብሮ እስኪጠናቀቅ የሚዘጉ መንገዶች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበረው የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታ አካላት ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡
 
የምስጋና ፣ የፍቅር ፣ የሰላምና የይቅርታ በዓል የሆነው እና በዓለም የትምህርት ፣ ሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በማይዳሰሱ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው የገዳ ስርዓት አካል የሆነው የኢሬቻ በዓል በሃገራችን በብሄራዊ ደረጃ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡
 
በርካታ ህዝብ የሚታደምበት እና አባገዳዎች ፣ አደ ስንቄዎች ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሚገኙበት የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል መስከረም 21 ቀን 2015 ዓ/ም በልዩ ድምቀት በአዲስ አበባ ይከበራል፡፡ በዓሉ በሰላም እንዲከበር መላው የፀጥታ አካላት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡
 
የአዲስ አመትና እና የመስቀል በዓል አከባበር የነበሩ ጠንካራና ያጋጠሙ ክፍተቶች ተለይተው ለኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል በሰላም መከበር ጠቃሚ ግብዓቶች መወሰዳቸውንም ግብረ ኃይሉ ጨምሮ ገልጿል፡፡
 
ከዚህም በተጨማሪ ለወንጀል መከላከል ተግባር ልዩ ትኩረት በመስጠት አብዛኛውን የሰው ኃይል በወንጀል መከላል ስራ ላይ መሰማራቱንና በዓሉ ወደ ሚከበርበት ስፍራ የሚመጡ ታዳሚዎች ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ መኖሩን ተገንዘበው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ጠይቋል፡፡
 
በያዝነው ዓመት በርካታ ህዝብ የታደመባቸው ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊና ብሄራዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ወሳኝ ስራ ማከናወኑን ግብረ ኃይሉ አስታውሶ የዘንድሮው የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል በሰላም እንዲከበር የበዓሉ ታዳሚዎች እና የከተማው ነዋሪ የተለመደውን ትብብራቸውን እንዲያደርጉ በፀጥታ አካለት ስም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
 
በተመሳሳይ የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል ተከብሮ እስከሚጠናቀቅ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር እና አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገድን እንዲጠቀሙ ዝግ የሚደረጉ መንገዶችን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
 
በዚህም መሰረት፡-
 
• ከቦሌ አየር መንገድ በሚሊኒዬም አዳራሽ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ወሎ ሰፈር አደባባይ
 
• ከመገናኛ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ 22 ማዞሪያ
 
• ከ4ኪሎ በውጭ ጉዳይ ሚ/ር ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኮንሰን መስቀለኛ ወይም ወዳጅነት ፓርክ
 
• ከፒያሳ በቸርቸር ጎዳና ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቴዎድሮስ አደባባይ
 
• ከጦር ሃይሎች በለገሃር ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት
 
• ከጀሞ በትንባሆ ሞኖፖል ወደ ሜክሲኮ የሚወስደው መንገድ አፍሪካ ህብረት አደባባይ
• ከቄራ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ የሚሄደው መንገድ ቡልጋርያ ማዞሪያ
 
• በአዲሱ መንገድ ከቄራ በቂርቆስ ወደ ለገሃር የሚወስደው መንገድ ታቦት ማደሪያ
 
• ከሳሪስ ፣ በጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ጎተራ ማሳለጫ
 
• ከቦሌ ወደ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን የሚወስደው መንገድ አትላስ ሆቴል አካባቢ
 
• ከአዋሬ ወደ ካሳንቺዝ የሚወስደው መንገድ ሴቶች አደባባይ
 
• ከልደታ በጌጃ ሰፈር ፣ ጤና ጥበቃ የሚወስደው መንገድ አብነት ፈረሰኛ ፖሊስ አካባቢ
 
• ከመርካቶ በጎማ ተራ ወደ አምስተኛ የሚወስደው መንገድ በርበሬ በረንዳ
• ከመርካቶ በራስ ቴአትር ወደ ጎማ ቁጠባ ተክለ ሃይማኖት አደባባይ
 
ከአርብ መስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ ፕሮግራሙ እስከሚጠናቀቅ ድረስ መንገዶቹ ለጊዜው ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ፡፡
 
በዓሉ በሚከበርበት ዙሪያ እና በአካባቢው በግራና በቀኝ ለረጅም ሆነ ለአጭር ጊዜ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡
 
በመጨረሻም ህብረተሰቡ የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት መረጃ ለመስጠት በ991 ወይም 816 ነፃ የስልክ መስመሮችን እና 01- 11 -11- 01 -11፣ 01- 11- 26- 43- 59፣ 01- 11- 01- 02- 97፣ መጠቀም እንደሚችል እና ለፀጥታው ስራ ስኬታማነት ህብረተሰቡ እያደረገ ላለው ቀና ትብብር የአዲስ አበባ ፖሊስ በመላው የፀጥታ አካላት ስም ምስጋናውን እያቀረበ በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.