Fana: At a Speed of Life!

ኢሬቻ ባህላዊ እሴቶቹ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት -የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢሬቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ግንባታና አብሮነት ዓይነተኛ ሚና ያለው ቅርሳችን በመሆኑ ባህላዊ እሴቶቹ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የኢሬቻ በዓልን አስመልክቶ ለመላ ኢትዮጵያውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ኢሬቻ ለህብረብሔራዊ አንድነት ግንባታና አብሮነት ዓይነተኛ ሚና ያለዉ ቅርሳችን በመሆኑ ባህላዊ እሴቶቹ ተጠብቀዉ ለትዉልድ እንዲተላለፍ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት!

በመጀመሪያ ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ/አደረሰን!

የኦሮሞ ህዝብ ክረምት አልፎ ፀደይ ሲመጣ፤ በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ ሲገናኝ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና ያቀርባል። ይህ ለብዙ ሺህ ዘመናት ሲከናወን የቆየ ሀገራዊ ትውፊት ነው፡፡ ይህ ትውፊት ኢሬቻ ነው፡፡

ኢሬቻ ፈጣሪ (ዋቃ) ለሰዉ ልጆች ለሰጠዉ የሚመሰገንበት ልዩ በዓል ነው፡፡ ኢሬቻ ‘ዝናብ አዝንቦ ለሰጠው ውሀ፤ እንዲበቅል ላደረገው አዝመራ፤ ከክረምት ጨለማ ወደ ብራ (ፀሓያማ ወቅት) ስላሸጋገርከን እናመሰግናለን’ እየተባለ ፈጣሪ የሚመሰገንበት በዓል ነው፡፡

ኢሬቻ ምስጋና ብቻ ሳይሆን የአንድነት፣ የወንድማማችነት፣ የእርቅና የሰላም በዓልም ነው፡፡ የኢሬቻ ቀን ከመድረሱ በፊት የተቀያየመ፣ የተጣላ ሁሉ ታርቆ፣ ይቅር ተባብሎ ቂም-በቀልን አስወግዶ፤ በኢሬቻ ቀን ፈጣሪውን እያመሰገነ ከወዳጅ ዘመዶቹ ጋር በዓሉን ያከብራል፡፡ ይህ የኢሬቻ ባህላዊ እሴትና አከባበር ሥነ_ስርዓት በአገራችን ወንድማማችነት እንዲጠናከር፣ አብሮነት እንዲጎለብትና ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥ ከፍተኛሚና ይጫወታል፡፡

ኢሬቻ ከማመስገን አልፎ አንድነት የሚፀናበት ሀገራዊ ሀብት ነው፡፡ በኢሬቻ ዕለት ከተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች በተጨማሪ ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የሚሳተፉ የአንድ ሀገር ልጆች በአንድነት የሚሰባሰቡበት፤ በፍቅር የሚደምቁበትና የሚጠያየቁበት በዓል ነው፡፡

ኢሬቻ በአንድ ቦታ፤ የአንድ ሀገር ልጆች ተሰባስበው ሀገራዊ እሴታቸውን የሚያዳብሩበት የህብረትመገለጫም ነው፡፡ ኢሬቻ እንደ ሀገር ካሉን ቅርሶች አንዱ ሲሆን የማይዳሰስ ቅርስ ተደርጎ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት ዩኔስኮ የተመዘገበዉ የገዳ ሥርዓት አካል ተደርጎ የተመዘገበ የሀገር ሃብትም ጭምር ነዉ፡፡

ኢሬቻ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚታደሙት ከመሆኑም በላይ ሴቶች፤ ወንዶች፤ ህጻናት፤ ወጣቶች፤ ሽማግሌዎች፤ አባገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች በውብ አለባበስ ደምቀው የሚያከብሩት የውበት በዓል በመሆኑ ከፍተኛ የቱሪዝም ሃብታችን እየሆነ ነዉ፡፡

አደይ አበባ እና እርጥብ ሳር ተይዞ በአባ ገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች ‘መሬሆ’ እየተባለ ውብ ዝማሬ የሚሰማበት የኢሬቻ በዓል የተለያዩ አካባቢ ወጣቶች ባህላዊ ጭፈራ እና ዘፈን የሚያሳዩበት ባህላዊ የጥበብ መድረክም በመሆን ከአገር ዉስጥና ከውጭ በርካታ ቱሪስቶችን በመሳብ ለአገር ኢኮኖሚ መነቃቃት ከፍተኛ ድርሻ ይጫወታል፡፡

ይህ ባህላዊ እና የውበት መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል ከሀገር አልፎ የዓለም ሀብት በመሆኑ፤ የቱሪዝም ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል ስርአቱን በጠበቀ መንገድ ማክበር ያስፈልጋል፡፡ የበዓሉ እሴት ሳይበረዝ እንዲቀጥል የበዓሉ ባለቤት የሆነው መላው ህዝብ የበዓሉን እሴት ሳይለቅ እንደሌላው ጊዜ ሁሉ በፍቅር፤ በሠላምና በአንድነት እንዲያከብረው መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

መልካም የኢሬቻ በዓል!

መስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.