Fana: At a Speed of Life!

የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከባድ የግድያ፣ የውንብድና እና የዘረፋ ወንጀልን ሲፈጽሙ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር መዋላቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገለፀ።
 
የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው በንፁሃን ዜጎች ላይ ሦስት(3) የግድያ፣ አንድ(1) የመግደል ሙከራ፣ አርባ ስድስት(46) በጦር መሣሪያና በድምጽ አልባ የስለት መሣሪያዎች የታገዘ የዘረፋና የውንብድና ወንጀሎችን በመፈፀም ሕብረተሰቡ በሥጋት እንዲኖር ሲያደርጉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የጋራ ግብረ-ኃይሉ ገልጿል፡፡
 
ከህወሓት የሽብር ቡድን ጋር በመቀናጀት በአዲስ አበባ ከተማ፣ በሞጆ፣ በዝዋይ፣ በሻሸመኔ፣ በቱሉቦሎ፣ በወሊሶ፣ በቡታጅራና በወልቂጤ በሚወስዱ መንገዶች ላይ በአራት ቡድን ተደራጅተው የፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስና አንፀባራቂ ልብስ በመልበስ፣ ከፍተኛ የብርሃን ኃይል ያለው ባውዛ እና በጦር መሣሪያ በመታገዝ ተሽከርካሪዎችን እያስቆሙ ከባድ የዘረፋና የግድያ ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ የኦነግ ሸኔ አባላት፡-
 
1. አብደላ ከድር ፣
 
2. ቦና አያኖ ፣
 
3. ታሪኩ ሲርባ ፣
4. ቃሲም ገመቹ ፣
 
5. ዲታ ካሼ ፣
 
6. መሐመድ አደም፣
 
7. ጫላ ወንድሙና
 
8. ጀማል ከድር
 
የተባሉት ተጠርጣሪዎች የራይድ ተሽከርካሪዎችን በከፍተኛ ገንዘብ በመኮናተር ወደ ክልል ከተሞች በመውሰድ የተለያዩ ሰበቦችን በመፍጠር ካመሹ በኋላ በሌሊት ወደ አዲስ አበባ እንሂድ በማለት በጉዞ ላይ ሳሉ ጨለማና ጭር ያለ ቦታ ሲደርሱ አሽከርካሪውን በማስቆም የአሽከርካሪዎችን አንገት በስለት ወግቶ በመግደል በአሽከርካሪዎች ላይ አሰቃቂ ወንጀል መፈፀማቸውን ሁሉም ተጠርጣሪዎች አምነው የወንጀል ቦታውንና አፈፃፀማቸውን ለምርመራ ቡድኑ መርተው አሳይተዋል፡፡
 
በሽብር ተግባራት ላይ የተሰማሩት የህወሓትና የሸኔ የሽብር ቡድኖች በሀገር ላይ ግልጽ ጦርነት ከፍተው ንፁሃንን በጅምላ በመግደል ሕዝቡን ስሜት ውስጥ በማስገባት ሀገሪቱ ወደ ለየለት ብጥብጥ እንድትገባ ለማድረግ የሸረቡት ሴራ ሳይሳካላቸው ሲቀር በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የግድያና የዘረፋ ቡድኖች በማሰማራት የከተማ ውስጥ ሽብርና ጦርነት ለመፈጠር ሲቀንቀሳቀሱ እንደነበር ግብረ-ኃይሉ ደርሶባቸዋል።
 
የሽብር ድርጊቱ ተሳታፊዎች በፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ብርቱ ክትትልና በህብረተሰቡ መረጃ ሰጪነት ሁሉም የወንጀሉ ተሳታፊዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጾ አዲስ አበባ እና ሌሎች የሀገራችን ከተሞች ከመሰል የሽብር እና የወንጀል ድርጊቶች የመከላከልና ወንጀሎቹም ተፈጽመው ሲገኙ ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ሥር የማዋል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አሳስቧል፡፡
 
በተመሳሳይ ሁኔታ በሀረርና በድሬዳዋ በተለያዩ አካባቢዎች የአድራሻ ለውጥ እያደረገች የሸኔን የሽብር ቡድን በህቡዕ ስታደራጅ የነበረችው የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራር ጫልቱ መሐመድ አብዲ በቅጽል ስሟ (ጃል ቦንቱ ጉሚ) ተብላ የምትጠራው ተጠርጣሪ በኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን በኬኒያ ሶሎሎ የውትድርና እና የካድሬ ስልጠና ወስዳ ወደ ሽብር ቡድኑን ተቀላቅላ ጃል ገመቹ አቦዬ ከሚባል የሸኔ ሽብር ቡድን ከፍተኛ አመራር ጋር እየተገናኘች ወጣቶችን በመመልመል ወደ ኬኒያ ሶሎሎ ማሰልጠኛ እየላከች የሽብር ቡድኑን እንዲቀላቀሉ በማድረግና ኢትዮ-ኬኒያ ድንበር ድረስ በመዘዋወር ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የሽብር ተግባር ስትፈጽም ቆይታ በቅርቡ በተደረገው ኦፕሬሽን በድሬዳዋ ከተማ ከ13 ግብረ አበሮቿ እና ኤግዚቢቶች እንዲሁም ከተለያዩ ሚስጥራዊ ሰነዶች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋሏን ግብረ-ኃይሉ ገልጿል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.