Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ቢዩልደርስ አዋርድስ አቶ አይሸሽም ተካን ሸለመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አይሸሽም ተካ በአፍሪካ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ቢውለደር አዋርድስ ሽልማት አበረከተላቸው፡፡

የአፍሪካን ኢኮኖሚ በመገንባት ትልቅ ድርሻ ላበረከቱ ታዋቂ አልሚዎች እውቅና የሚሰጠው “የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ቢዩልደርስ” ሽልማት÷ ዘንድሮ ለኢትዮጵያዊው ባለሀብት አይሸሽም ተካ እና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለተወጣጡ 30 አልሚዎች እውቅና ሰጥቷል።

12ኛው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ቢዩልደር ፎረምና አዋርድስ “በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ዘመን የኢኮኖሚ ውህደት” በሚል መሪ ቃል ትናንት ማምሻውን በኮትዲቭዋር አቢጃን ተካሄዷል።

በመርሐግብሩ ላይ ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አይሸሽም ተካ በኢትዮጵያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት በምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ላደረጉት አበርክቶ ሽልማት አግኝተዋል።

ባለሀብቱ ሽልማቱን ከቀድሞ የኮትዲቭዋር ጠቅላይ ሚኒስትር ፓስካል አፊ ንጉዌሳን እጅ ተቀብለዋል።

አቶ አይሸሽም ተካ በቀን ሠራተኝነት ሰባት ብር ደመወዝ ተቀጥረው ሥራን ሳይንቁ በመስራት ወደ ባለሀብትነት መሸጋገራቸው በሽልማቱ ስነ ስርዓት ላይ ተገልጿል።

ላለፉት 15 ዓመታት ኑሯቸውን በደቡብ ሱዳን በማድረግ የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን እያከናወኑ የሚገኙት ባለሀብቱ÷ በጁባ ቆይታቸው በሰላም፣ ልማትና ሰብዓዊ ድጋፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በፈረንጆቹ በ2019 ከደቡብ ሱዳን መንግሥት የክብር ዜግነት ተሰጥቷቸዋል።

አቶ አይሸሽም ባደረጉት ንግግር÷ ከቀን ሠራተኝነት ተነስቶ በጠንካራ የሥራ ትጋት በአፍሪካ ምጣኔ ሀብት ዕድገት አስመዝግቦ መሸለም መቻል ለአፍሪካውያን ወጣቶች ተምሳሌት ይሆናል ብለዋል፡፡

ሽልማቱ በቀጣይ ጠንከረው እንዲሠሩ ተጨማሪ ኃላፊነት ጥሎብኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.