Fana: At a Speed of Life!

ኢሬቻ የኦሮሞ ታላቅነት የሚታይበት መድረክ የሰላምና ወንድማማችነት ምልክት ነው- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢሬቻ የኦሮሞ ታላቅነት የሚታይበት መድረክ የሰላምና ወንድማማችነት ምልክት ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኢሬቻን በዓል አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ባህል የማንነት መገለጫ የኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ስርዓት እንዲሁም የአመጋገብና አለባበስ ስርዓት መገለጫ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የሐዘንና የደስታ እንዲሁም የአምልኮ ስርዓትን የሚያመለክት መሆኑን ጠቅሰው÷የባህል እድገት ከማህበራዊ ለውጥ ጋር ስለሚመጋገብ የሁሉም እድገት ባህል ነው ማለት እንችላለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ የዓለም ፍልስፍና የሚረዳና ለአኗኗር ትርጉም የሚሰጥ ህዝብ መሆኑንም በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ  ባህል ለትውልድ እንዲሻገር የሚያደርግ ጠንካራ ስርዓት የዘረጋ ህዝብ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ከፈጣሪ ጋር ያለው መቀራረብ ስርዓት ያለውና የራሱን የዘመን አቆጣጠር መተንበይ የቻለ፣ ዘመናዊ የአስተዳደር ስርዓት ለዓለም ያበረከተ ታላቅ ህዝብ ነው ብለዋል፡፡

̎እንደ ኦሮሚያ ክልል ኦሮሞ ወደ የጥንቱ ባህሉ መመለስ አለበት ስንል አባቶቻችን ትናንት በዘረጉት መሰረት አጥንተን በእውቀት የታጀበ ለትውልዱ ዋስትና የሆነ ስርዓት ማረጋገጣችን ነው̎ ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

ባህልን ማበልጸግ፣ ጥበብን ማሳደግ፣ ቋንቋን ማልማት የህብረተሰብን አኗኗር በማሻሻል ተወዳዳሪ ትውልድ ማፍራትና ፈጠራን በማስፋፋት የኦሮሚያ ክልል ማህበራዊ ልማት ግቦች ላይ  ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢሬቻ ባህል፣ ታሪክና ፈጣሪ የሚመሰገንበት ታላቅ፣ ታናሽ፣ አዛውንት፣ ወንድና ሴት ሳይል በአንድነት ወደ ወንዝና ተራራ ወጥቶ እርቅ፣ ይቅርታ መልካም ምኞትና ስኬት፣ ሰላምና ብልጽግና እንዲሁም አንድነት የሚበሰርበት ታላቅ የኦሮሞ ክብረ በዓል ነው ብለዋል፡፡

ኢሬቻ የሰላና የእርቅ ምልክት ነው ያሉት አቶ ሽመልስ አብዲሳ÷ ̎የፈጣሪና ምድር፣ የፈጣሪና ፍጥረታት እርቅ የሚበሰርበት ቦታም ነው ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡

̎ሰው ከሰው ጋር ከታረቀ ነው ፈጣሪም ከሰው ጋር የሚታረቅ̎ የሚባለው፣ ስለዚህ በኦሮሞ ባህል ቂም በቀል ተይዞ ወደ ̎መልካ̎ (ወንዝ) አይኬድም ነው ያሉት።

ኦሮሞ ወደ ̎መልካ̎ ሲሄድ ጥላቻን በፍቅር፣ ቂምን በይቅርታ አልፎ ሲገነባ የነበረው  ጠንካራ የማህበራዊ ግንኙነት ለመግለጽ መሆኑንም አንስተዋል።

ኦሮሞ ወደ ጥንቱ ባህሉ ተመልሶ የተጣላ በማስታረቅ የሰላምና እርቅ መንገድንም እንደሚመርጥ ጠቅሰው÷ ሰላምና እርቅን የኑሯችን መሰረት አድርገን በመካከላችን ሰላም ለመፍጠር ይቅር መባባል አለብንም ነው ያሉት፡፡

ኢሬቻ የኦሮሞ ታላቅነትን የሚያሳይ፣ የብሔር ብሔረሰቦች አንድነትና ወንድማማችነት ምልክት መሆኑን ጠቅሰው÷ ባለፉት ስርዓት ተቀብሮ ተደብቆ ቢቆይም በተደረገ ተጋድሎ የተደበቀ ባህል ወጥቶ የተረሳ ታሪክ ተመልሷል ብለዋል፡፡

በተለይ የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ ከ150 በላይ አመታት ተቋርጦ የነበረ የኦሮሚያ ክልል ከህዝቡ ጋር በሰራው ሥራ ተመልሷል ሲሉ በመልዕክታቸው ገልጸዋል፡፡

ጠንካራ ስርዓት ያለው ህዝብ ባህሉን እና ታሪኩን ይጠብቃል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በድጋሚ ባህሉ ቋንቋው እንዳይጨቆን በፅኑ መሰረት ላይ ይገነባል ብለዋል በመልዕክታቸው።

በዚህም ታሪክ ፣ባህል እና እሴቱ ጠንካራ ስርዓት እንዲሆን እየተሰራ ባለ ስራ የኦሮሞ ባህል ወደ ነበረበት እየተመለሰ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡

የገዳ ስርዓት አካል የሆነና መንግስት በትኩረት እየሰራበት ያለው የባህላዊ ፍርድ ቤት በመላ ኦሮሚያ  ተዋቅሮ ህዝቡ ፍትህን በቀዬው ማግኘት መቻሉ የጥንቱ እሴቱ ስርአት መሆኑ ማሳያ መሆኑንም ነው ያመላከቱት፡፡

ፈጣሪ የሰጠንን ፍቅር ተጠቅመን በይቅርታ እርቅ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የትናንቱ  ቂም ይቅርታ የዛሬውን አለመግባባት  በእርቅ ፈተን ጠንካራና የበለፀገች ሀገር በአንድነት ለመገንባት የሀገራዊ ምክክር ሂደት እውን ለማድረግ ሁሉም የሚጠበቅበትን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ኢሬቻ የዓለም ሃብት ቱሪዝም ምንጭ የኦሮሞ ባህል በዓለም ሲተዋወቅ በሰላም እና ባማረ መልክ እንዲሁም ሌሎች ብሄርብሄረሰቦችን ባሳተፈ መልኩ እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉ የሰላም እና የስኬት እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.