የሀገር ውስጥ ዜና

የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ከ20 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ለጤና ተቋማት ድጋፍ አደረገ

By Melaku Gedif

September 30, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ከ20 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ በክልሉ ለሚገኙ ጤና ተቋማት ድጋፍ አድርጓል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ እንዳሉት÷ የተደረገው ድጋፍ በክልሉ ያለው የጤና አገልግሎት በተለይም የእናቶችና ህፃናትን ጤና አገልግሎት ለማሻሻል እንዲሁም የጤና መድህን ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎችን የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል።

ለዚህም የግብዓት እጥረት ያለባቸውን ተቋማት በጥናት በመለየት ክፍተቱን መቅረፍ የሚያስችል የህክምና ቁሳቁስ አከፋፍለናል ነው ያሉት።

የተደረገው ድጋፍ አልትራሳውንድ፣ የሆስፒታል አልጋና ሌሎች የላቦራቶሪ መሳሪያዎችን ያካተተ መሆኑ ተጠቁሟል።

መሳሪያዎቹ ለታለመላቸው አላማ በማዋል ህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ስልጠና መስጠት እና ክትትል ማድረግ ይገባል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ድጋፉ ለ15 የጤና ተቋማትና ሆስፒታሎች የተደረገ ሲሆን÷ የህክምና ቁሳቁሶቹም ከጤና ሚኒስትር፣ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩትና ከለጋሽ አካላት የተገኘ መሆኑን ተጠቁሟል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!